በሞባይል ስልክዎ ላይ ከእርስዎ ፈቃድ ውጪ የሚሰሩ ጉልበታም መተግበሪያዎች አሉ?
አዲሱ የመረጃ መንታፊዎች ረቂቅ ስልት
የእጅ ስልካችን ወይም ሞባይላችን በየዕለቱ አያሌ ስራዎችን እናቀላጥፍበታለን፡፡ የአንድ ሰው የእጅ ስልክ አጠቃቀም ሪፖርት ማለት የቀን ውሎው አቻ ሪፖርት እስከ መሆንም እየደረሰ ይገኛል፡፡
ይህን የተረዱት የመረጃ መንታፊዎች የቀደመ ስልታቸውን በመተው አዳዲስ ስልቶችን እየተጠቀሙ እንደሆነ በአሜሪካ የማሳቹሴትስ ዩንቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ያስጠናውን ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡
መረጃ መንታፊዎች በተለይም የእጅ ስልክ ተጠቃሚዎችን ኢላማ የሚያደርጉት በሚጠቀሟቸው መተግበሪያዎች ወይም አፕሊኬሽኖች አማካኝነት እንደሆነም በዚሁ ጥናት ላይ ተጠቅሷል፡፡
ለአብነትም የፎቶ ማቀነባበሪያ ፣ ለደህንነት ማረጋገጫ በሚል የተሰሩ መተግበሪያዎችን ስንጠቀም የሚፈልጉት መረጃ ወደ መንታፊዎቹ በቀጥታ አልያም በተዘዋዋሪ ይደርሳቸዋል ተብሏል፡፡
ለመረጃ ምንተፋ ተብለው የሚሰሩት እነዚህ መተግበሪያዎች በሞባይል ስልኮች ላይ ሲጫኑ ያለ ባለቤቶቹ ፈቃድ እንደ ስልክ ቁጥሮች፣ የአሻራ መረጃዎች፣ አዘውትረው የሚጠቀሟቸው መተግበሪያዎች፣ የገንዘብ እንቅስቃሴ፣ ግላዊ የሆኑ ጥብቅ መረጃዎች፣ የይለፍ ቃሎች እና ሌሎችንም መረጃዎች ይቆጣጠራሉም ተብሏል፡፡
በመሆኑም ሰዎች በስልኮቻቸው ላይ ያሉ መተግበሪያዎችን በየጊዜው ማረጋገጥ፣ ያልተገባ የመረጃ ፈቃድ መሰጠቱን እና ከፈቀዋድዎ ውጪ በስልክዎ ላይ የተጫኑ ጉልበታም መተግበሪያዎች ካሉ መፈተሸ እና ማስወገድ ይኖርቦታል ሲሉ ተመራማሪዎቹ አሳስበዋል፡፡
አሜሪካ ለአንድ መረጃ አሾላኪ 279 ሚሊዮን ዶላር ከፈለች
ከዚህ በተጨማሪም በእጅ ስልክዎት ላይ ያሉ መብራቶች እርስዎን ለመሰለል ሊውሉ ይችላሉ የተባለ ሲሆን እነዚህ መተግበሪያዎች ከሚጠበቅባቸው አገልግሎት ባለፈ ተጨማሪ ፈቃድ እንዲሰጡ ሲጠየቁ ፈቃድ መከልከል እንደሚገባም ተገልጿል፡፡
ብዙ የእጅ ስልክ ተጠቃሚዎች የሚሰረቅ መረጃ የለኝም ብለው ይዘናጋሉ የሚሉት እነዚህ የቴክኖሎጂ ተመራማሪዎች ዘመናዊ ስልክ የሚጠቀም ሁሉ ያለ ፈቃድዎ ፍላጎትዎን በማጥናት ብቻ የእርስዎን ትኩረት ሊስቡ የሚችሉ ማስታወቂያዎች እንዲደርስዎት ለቴክኖሎጂ ኩባያዎች ሊሸጥ የሚችል መረጃ እንዳለ ማወቅ ይኖርብዎታል ብለዋል፡፡