የታዋቂ እጽ አዘዋዋሪው ስመ ሞክሼ ኮሎምቢያዊ ለሶስተኛ ጊዜ ታሰረ
የ46 አመቱ ሬኔ ማርቲኔዝ ጉቴሬዝ ከታዋቂው የፔሩ እጽ አዘዋዋሪ ጋር ስሙ መመሳሰሉ ዋጋ እያስከፈለው ነው
ጉቴሬዝ ከሰሞኑም የታመመ አባቱን ለመጠየቅ ወደ ኮሎምቢያ እንዳመራ በቁጥጥር ስር ውሏል
ኮሎምቢያው ግለሰብ ስሙ ደጋግሞ የማረሚያ ቤት ደጅን እንዲረግጥ አስገድዶታል።
የ46 አመቱ ሬኔ ማርቲኔዝ ጉቴሬዝ ከፔሩ የእጽ አዘዋዋሪ ስም መጋራቱ ባለፉት 13 አመታት ውስጥ ሶስት ጊዜ ታስሯል።
ምንም አይነት የወንጀል ሪከርድ የሌለበት ጉቴሬዝ በአለም አቀፍ ደረጃ በወንጀል ተፈላጊ ከሆነው የፔሩ ተወላጅ እጽ አዘዋዋሪ ጋር ስም መጋራቱ ወንጀል ሆኖበት ኢንተርፖል ያሳድደው ይዟል።
በፈረንጆቹ 2010 በኮሎምቢያ ቦጎታ የንግድ ስራ ለመጀመር ፈቃድ ለማውጣት ከፖሊስ ማስረጃ ለማምጣት ባመራበት ወቅት ነው ለመጀመሪያ ጊዜ በቁጥጥር ስር የዋለው።
ንግድ ለመጀመር ከወንጀል ነጻ ድብዳቤን ለማውጣት ያመራው ጉቴሬዝ፥ አለም አቀፍ የወንጀል ተፈላጊ ነህ ተብሎ ለስምንት ቀናት ታስሮ ተለቋል።
በኮሎምቢያ ወደሚገኘው ኤምባሲ እና ኢንተርፖል በማምራት ምን እንደተፈጠረ ሲጠይቅም፥ የስም ግጥምጥሞሹ ያመጣበት ፈተና እንደሆነ ይነገረዋል።
ከአንድ አመት በኋላም የስራ ቦታው ተዘርፎ ለምስክርነት ወደ ቦጎታ ፖሊስ ጣቢያ ሲያመራ ለዳግም እስር መዳረጉ ሌላ ግርምትን መፍጠሩን ኦዲቲኢ ሴንትራል አስታውሷል።
በዚህኛው የእስር ጊዜም ጉዳዩ ይጣራ በሚል ለሁለት ወራት ታስሮ ተፈላጊው ወንጀለኛ አለመሆኑ ተረጋግጦ ወጥቷል።
ይህም ጉቴሬዝ ከወንጀል ተጠርጣሪነት ነጻ ለመሆን ሀገር ጥሎ መውጣትን እንዲመኝና በ2012 ቤተሰቦቹን ይዞ ወደ አሜሪካ እንዲሰደድ አደረገው ይላል ዘገባው።
ከ11 አመት በኋላ ወደ ሀገሩ ኮሎምቢያ ባለፈው ወር የታመሙ አባቱን ለመጠየቅ ሲመለስም ይሄው ስሙ ያመጣበት መጥፎ እድል አልለቀቀውም።
ሬኔ ማርቲኔዝ ጉቴሬዝ አውሮፕላኑ የቦጎታን መሬት እንደረገጠ በኢንተርፖል መታወቂያውን እንዲያሳይ ተጠይቆ ለሶስተኛ ጊዜ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲያመራ ተገዷል።
እስካሁንም በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት ይገኛል ተብሏል።
ይበልጥ አሳዛኙ ነገር ግን ጉቴሬዝ የታመሙ አባቱን ሳያያቸው ህይወታቸው የማለፉ ዜና ነው።
የፔሩ መንግስት ኮሎምቢያዊው ሬኔ ማርቲኔዝ ጉቴሬዝ በአደንዛዥ እጽ ዝውውር የሚፈለገው የፔሩ ዜጋ አለመሆኑን ማረጋገጫ በመስጠት እንዲፈታም የጉቴሬዝ ቤተሰቦች በመወትወት ላይ ናቸው።