አሜሪካ በ2025 ከቻይና ጋር ጦርነት ውስጥ ልትገባ ትችላለች - የአሜሪካ ጀነራል
ፔንታጎን ግን የአሜሪካ አየር ሃይል ባለአራት ኮከብ ጀነራሉ ማይክ ሚንሃን ያነሱት ስጋት ከግምገማችን ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም ብሏል
ሁለቱ ሀገራት በታይዋን ጉዳይ የገቡበት ፍጥጫ ግን አሁንም አልበረደም
አሜሪካ በቀጣዮቹ ሁለት አመታት ውስጥ ከቻይና ጋር ጦርነት ውስጥ ልትገባ እንደምትችል የአሜሪካ ጀነራል አስጠንቅቀዋል።
የአሜሪካ አየር ሃይል ባለአራት ኮከብ ጀነራሉ ማይክ ሚንሃን ናቸው ዋሽንግተን በ2025 ከቤጂንግ ጋር ልትዋጋ እንደምትችል ስጋታቸውን ያነሱት።
የአየር ትራንስፖርት እና ተያያዥ አገልግሎቶችን የሚሰጠውና ከ110 ሺህ በላይ አባላት ያሉትን ተቋም የሚመሩት ጀነራል ማይክ አስተያየት ግን በፔንታጎን የአሜሪካ አቋም አይደለም ተብሏል።
የሀገሪቱ መከላከያ ሃይል ባለስልጣናት የጀነራል ማይክ ስጋት ከዋሽንግተን የስጋት ግምገማ አንጻር የሚስማማ አይደለም ማለታቸውንም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የፔንታጎን ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀነራል ፓትሪክ ሬይደር በሰጡት ምላሽ ከቻይና ጋር ያለው ወታደራዊ ፉክክር አሳሳቢነቱን አልደበቁም።
ይሁን እንጂ የአሜሪካ ዋነኛ ትኩረት የኢንዶ ፓስፊክ ቀጠናን ሰላማዊ፣ ነጻ እና ክፍት ለማድረግ ከአጋር ሀገራት ጋር መስራት ነው ሲሉም ገልጸዋል።ይሁን እንጂ ሀገራቱ በታይዋን ጉዳይ የገቡበት ፍጥጫ እያየለ መሄዱን ተንታኞች ይናገራሉ።
በ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሚያደርጉት ቻይና እና አሜሪካ የታይፒን ጉዳይ ትልቅ የምርጫ ቅስቀሳቸው አጀንዳ እንደሚያደርጉት ይጠበቃል።
በተለይ ዋይትሃውስ ለመግባት በሚደረገው ፉክክር ታይፒ ተደጋግማ መነሳቷ እንደማይቀር ነው የሬውተርስ ዘገባ ያነሳው።
ይህም ቤጂንግ የሉአላዊ ግዛቴ አካል ናት በምትላት ታይዋን ላይ ወታደራዊ እርምጃ በመውሰድ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እንድትንቀሳቀስ ሊገፋፋት እንደሚችል ነው ጀነራል ማይክ ሚንሃን የገለጹት።
የሚወሰደው ወታደራዊ እርምጃም አሜሪካ እና ቻይናን ወደለየለት ጦርነት ይከታል የሚልም ስጋታቸውን በጻፉት ደብዳቤ አጋርተዋል።
ዓለም አቀፉ የስትራቴጂክ ጥናት ማዕከል በቅርቡ ይፋ ያደረገው ጥናት ግን አሜሪካ በቻይና ላይ ጦርነትን ለመክፈት በቂ የመሳሪያ ክምችት እንደሌላት ያመላክታል።
አሁን ላይ አሜሪካ ከቻይና ጋር ወደ ጦርነት ብታመራ ከአንድ ሳምንት በላይ መዋጋት እንደማትችል በጥናቱ ላይ መጠቀሱም አይዘነጋም።