የኤርትራ ወታደሮች አሁንም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንደሚገኙ አሜሪካ ገለጸች
የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ፤ አሁንም በሺዎች የሚቀጠሩ ኤርትራ ወታደሮች በትግራይ አሉ ብለዋል
የመከለከያ የውጭ ግንኙነት ኃለፊው ሜ /ጀነራል ተሾመ ገመቹ በትግራይ ከመከላከያ ውጭ በትግራይ በግዳጅ ላይ ያለ የጸጥታ ኃይል የለም ብለዋል
ለሁለት አመታት በዘለቀው ደም አፋሳሹ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር ሆነው የትግራይ ታጣቂዎችን ሲዋጉ መቆየታቸው በተለያዩ ጊዜያት ሲነሳ የቆየ ጉዳይ ነው፡፡
ከወራት በፊት በተደረሰው በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሰነድ ድንጋጌ መሰረትም ከሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ውጪ የሆኑ ኃይሎች ከትግራይ ክልል መውጣት እንዳለባቸው ተመላክቷል፡፡
ከክልሉ እንዲወጡ ከሚጠበቁት ኃይሎች የኤርትራ ወታደሮች ዋናኛ መሆናቸውም ቢገለጽም የወታደሮች ከትግራይ የመውጣት ጉዳይ አወዛጋቢ ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡
የመከለከያ ሰራዊት የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ ከትናንት በስትያ በአዲስ አበባ ለወታዳራዊ አታሼዎች ማብራሪያ ሲሰጡ በትግራይ ከመከላከያ ሰራዊት ውጭ ሌላ የጸጥታ ኃይል የለም ብለዋል፡፡
ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ "በትግራይ ክልል ከኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት በስተቀር በግዳጅ ላይ ያለ ሌላ የጸጥታ ሃይል የለም" ብለዋል፡፡
ሜጀር ጀነራሉ ይህን ይበሉ እንጅ የኤርትራ ወታደሮች አሁንም በኢትዮጵያ ግዛት ስለመኖራቸው በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ ተናግረዋል፡፡
ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ በቅርቡ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በሰጡት በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ "የኤርትራ ወታደሮችን በተመለከተ ወደ ድንበር አከባቢ እንደተመለሱ እንዲሁም ለቀው እንዲወጡ መጠየቃቸውን እናውቃለን" ማለታቸው ሮይተርስ ዘግቧል።
አምባሳደሯ የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ ስለመኖራቸው በማስረጃነት ወይም ምንጭነት የጠቀሱት ነገር ግን የለም፡፡
የህወሓት ቃል አቀባዩ ጌታቸው ረዳ የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ወጥተዋል የሚለውን የሜጀር ጀነራሉን ኃሳብ ውድቅ አይቀበሉም፡፡
“በሺዎች የሚቀጠሩ ኤርትራ ወታደሮች አሁንም በትግራይ ይገኛሉ” ሲሉም ነው ቃል አቀባዩ በትዊተር ባጋሩት ጽሁፋቸው የተናገሩት፡፡
ኤርትራ በአምባሳደር ሊንዳ እና ቃል አቀባዩ ጌታቸው ዙሪያ አስተያየት ዙሪያ ያለችው ነገር የለም፡፡
የኤርትራ ወታደሮች ባሳለፍነው ሳምንት ከነበለት፣ አድዋ ፣ አክሱም እንዲሁም ሽሬ መውጣታቸው የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡት የነበረ ነው፡፡
ይሁን እንጅ አል-ዐይን አማርኛ የኤርትራ ወታደሮች የወቅቱ እንቅስቃሴን መነሻ በማድረግ ያናገራቸው የትግራይ ክልል ነዋሪዎች አሁንም የኤርትራ ወታደሮች ይወጣሉ ብለው ለማመን እንደሚቸገሩ መናጋራቸው አይዘነጋም፡፡
የኤርትራ ወታደሮች እንቅስቃሴ ለዓለም አቀፍ ተቋማት የ“እየወጣን ነው” መልእክት ለማስተላለፍ ሊሆን እንደሚችልም ያላቸውን ጥርጣሬ አስቀምጠው ነበር ነዋሪዎቹ፡፡
ነዋሪዎቹ ከመሃል አካባቢ ሰወጡ “እኛ እንዲህ ነን” የሚል ዛቻ ያሰሙ ነበር ሲሉም ተናግረው ነበር፡፡