ቱርክ በአሜሪካ የሚገኙ ዜጎቿን “እስልምና ጠል” ከሆኑ ጥቃቶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ አስጠነቀቀች
ሰሞኑ በአውሮፓ ቁርዓን የተቃጠለበት አሳዛኝ ድርጊት አንካራን እጅጉን አስቆጥቷል
ቱርክ፤ "የጸረ እስልምና እና ዘረኝነት ድርጊቶች" በአውሮፓ ያለውን የኃይማኖት አለመቻቻል ማሳያ ናቸው ብላለች
ቱርክ በአሜሪካ አውሮፓ የሚገኙ ዜጎቿን ከተለያዩ ጥቃቶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል አስጠነቀቀች፡፡
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአሜሪካ እና በአውሮፓ ሀገራት ያሉ ዜጎቹን "ሊደርሱ ከሚችሉ የውጭ ዜጋ ጥላቻ ፣የዘረኝነት ትንኮሳ እና ጥቃቶችን ራሳቸውን ጠብቀው በተረጋጋ መንፈስ እንዲንቀሳቀሱ" እንዲሁም "ሰልፎች ከሚካሄዱባቸው ስፍራዎች እንዲርቁ" መክሯል ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመሩ ያሉ "የጸረ እስልምና እና ዘረኝነት ድርጊቶች" በአውሮፓ ያለውን የሃይማኖት አለመቻቻል እና የጥላቻ መጠን የሚያንጸባርቁ ናቸውም ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡
ቱርክ ይህን የማስጠንቀቂያ መግለጫ ያወጣቸው ምዕራባውያን አጋሮቿ በቱርክ የሽብር ጥቃት ሊከሰት ይችላል በሚል ዜጎቻቸውን ካስጠነቀቁ በኋላ መሆኑ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በአንካራ የሚገኙ የአሜሪካ፣ የጀርመን፣ የፈረንሳይ እና የጣሊያን ኤምባሲዎች አሸባሪዎች በቱርክ የአምልኮ ቦታዎች ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ እንደሚችሉ ጠቅሰው ዜጎቻቸው አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደረጉ አርብ እለት ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው፡፡
በተጨማሪም አንድ ጸረ እስልምና አክቲቪስት በኮፐንሃገን መስጊድ አቅራቢያ እና በዴንማርክ በሚገኘው የቱርክ ኤምባሲ ደጃፍ ላይ የሙስሊሞችን ቅዱስ መጽሐፍ (ቁርዓን) ቅጂዎች ማቃጠሉን አንካራን አስቆጥቷል፡፡
የዴንማርክ እና የስዊድን ዜግነት ያለው ራስሙስ ፓሉዳን በመባል የሚታወቀው አክቲቪስት ቀደም ሲል ጥር 21 ቀን በስዊድን ተመሳሳይ ድርጊት ፈጽሞ የነበረም ነው፡፡
አክቲቪስቱ ስዊድን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን እስክትቀላቀል ድረስ በየሳምንቱ አርብ ቁርዓንን የማቃጠል ድርጊቱ እቀጥልበታለሁ ማለቱም በስዊድን እና ቱርክ ያለው ውጥረት እንዳያባብሰው ተሰግቷል፡፡