ከሟቾቹ በተጨማሪ 198 ሰዎች ሲቆስሉ 50 ሺ ያክል ሰዎች ተፈናቅለዋል
በሱዳን የምዕራብ ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ አል ጂኔይና ፣ አረብ ነን በሚሉ እና አረብ አይደለንም በሚሉ በሁለት ጎሳዎች መካከል ከትናንት በስቲያ ጥር 08 ቀን 2013 ዓ.ም በተፈጠረ ግጭት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 129 መድረሱን የገዛቱ የዶክተሮች ሕብረት አስታውቋል፡፡
ሕብረቱ ዛሬ ጥር 10 በሰጠው መግለጫ ይፋ እንዳደረገው በአል ጂኔይና ከተማ በተካሔደው ደም አፋሳሽ ግጫት ከሟቾቹ በተጨማሪ 198 ሰዎችም ቆስለዋል፡፡
ተጎጂዎችን ለማከም የሕክምና ቁሳቁሶች እጥረት ከመኖሩም ባለፈ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አዳጋች መሆኑንም ሕብረቱ ገልጿል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ፣ በምዕራብ ዳርፉር የተከሰተው ግጭት እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል፡፡
ዋና ፀሐፊው ባወጡት መግለጫ ፣ በጎሳዎች መካከል እየተባባሰ ባለው ግጭት ከተከሰተው ሞት እና መፈናቀል በተጨማሪ 50 ሺ ያክል ሰዎች መፈናቀላቸውንም ገልጸዋል፡፡ የሱዳን ባለስልጣናት ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንዲወስዱም አሳስበዋል፡፡
የሀገሪቱ መንግስት የተፈጠረውን ሁኔታ በግልጽ የሚያጣራ ቡድን ወደ ስፍራው ልኳል፡፡
የዳርፉር አካባቢ ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት ያለበት ሲሆን በአካባቢው የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት እና የአፍሪካ ሕብረት ጥምር የሰላም አስከባሪ ኃይል ፣ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ተልዕኮውን አጠናቆ መውጣት ጀምሯል፡፡ ይህም አካባቢውን ለሌላ ቀውስ እንዳይዳርግ ስጋት ፈጥሯል፡፡ ለዓመታት በቆየው የዳርፉር ግጭት እና የሀር ማጥፋት ወንጀል ከ 300,000 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ ይገመታል፡፡