በሱዳን ምዕራብ ዳርፉር በተከሰተው ግጭት የሟቾች ቁጥር ወደ 48 ከፍ ብሏል
የሰላም አስከባሪዎች አካባቢዉን ለቀው በመውጣት ላይ መሆናቸው ለከፍተኛ ቀውስ እንዳያጋልጥ ተሰግቷል
ሐኪሞች የአል ጂኔይና ሆስፒታሎች ደህንነት እንዲጠበቅ ጥሪ አቅርበዋል
በሱዳን የምዕራብ ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ አል ጂኔይና ፣ አረብ ነን በሚሉ እና አረብ አይደለንም በሚሉ በሁለት ጎሳዎች መካከል በትናንትናው ዕለት ጥር 08 ቀን 2013 ዓ.ም በተፈጠረ ግጭት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ወደ 48 ከፍ ማለቱን የዶክተሮች ሕብረት አስታውቋል፡፡
ሕብረቱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ይፋ እንዳደረገው ከትናንት ጠዋት ጀምሮ በተካሔደው ደም አፋሳሽ ግጫት ከሟቾቹ በተጨማሪ 97 ሰዎችም ቆስለዋል፡፡
ትናንት የወጡ ዘገባዎች 32 ሰዎች ሲሞቱ እና 79 ሰዎች መቁሰላቸውን አመልከተው ነበር፡፡ ይሁንና ሕብረቱ ባደረገው የመጀመሪያ ማጣሪያ የሟቾች እና የተጎጂዎች ቁጥር ከፍ ማለቱን ነው የገለጸው፡፡
የህክምና ቁሳቁሶች እጥረት እና የእንቅስቃሴ ችግሮች ቢኖሩም ተጎጂዎችን ለመርዳት ሀኪሞች የሚችሉትን ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም መግለጫው ጠቅሷል፡፡
የሱዳን ዜና ወኪል እንደዘገበው በ አል ጂኔይና ከተማ የሚገኙ የጤና ተቋማት ጥበቃ እና የተለያዩ እገዛዎች እንዲደረጉላቸውም ሕብረቱ በሰጠው መግለጫ ጠይቋል፡፡
የዳርፉር አካባቢ ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት ያለበት ሲሆን በአካባቢው የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት እና የአፍሪካ ሕብረት ጥምር የሰላም አስከባሪ ኃይል ፣ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ተልዕኮውን አጠናቆ መውጣት ጀምሯል፡፡ ይህም አካባቢውን ለሌላ ቀውስ እንዳይዳርግ ስጋት ፈጥሯል፡፡ ለዓመታት በቆየው የዳርፉር ግጭት እና የሀር ማጥፋት ወንጀል ከ 300,000 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ ይገመታል፡፡