በደቡብ ዳርፉር “በጎሳ ግጭት” 15 ሰዎች ተገደሉ
በዳርፉር የሚገኘው የተመድ እና የአፍሪካ ሕብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል ከቀናት በኋላ እንዲወጣ ተወስኗል
ሱዳን በስፍራው ወታደሮቿን አሰማርታለች
በደቡብ ዳርፉር በተከሰተ የጎሳ ግጭት 15 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ትናንት እሁድ ዕለት የገለጹት አንድ የሱዳኑ ባለሥልጣን ፣ መንግሥት በስፍራው ተጨማሪ ኃይል ማሰማራቱን አስታውቀዋል፡፡
የሱዳን የዜና ወኪል የደቡብ ዳርፉር ገዥ ሙሳ ማህዲን ጠቅሶ እንደዘገበው ካርቱም በግዛቱ “በርካታ” ወታደሮችን ለማሰማራትም ተዘጋጅታለች፡፡
አካባቢው እ.ኤ.አ. ከ 2003 ጀምሮ ለበርካታ ጊዜያት መራራ ግጭት ሲያስተናግድ የቆየ በምዕራብ ሱዳን የሚገኘው የዳርፉር ግዛት አካል ነው ፡፡
በገሬይዳ ክልል በማሳሊትና በፋላታ ጎሳዎች መካከል ከውሃ ምንጭ ጋር በተያያዘ በተነሳ ግጭት ሁለት ፋላታዎችን የተገደሉ ሲሆን ፣ አንድ የአካባቢው መሪ እንዳሉት ፣ለዚሁ በወሰዱት የበቀል እርምጃ የፌላታ ጎሳ አባላት 13 ማሳሊቶችን በመግደል 34 ሰዎችን አቁስለዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት በሁለቱ ጎሳዎች መካከል በርካታ ደም አፋሳሽ ግጭቶች መከሰታቸውን የሱዳን ዜና ወኪል ዘግቧል ፡፡
በሁለቱ ጎሳዎች መካከል በጥቅምት ወር እርቅ ከተፈጸመ በኋላ በመካከላቸው ግጭት ሲነሳ ይህ የመጀመሪያቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የተባበሩት መንግስታት እና የአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በዳርፉር (UNAMID) ፣ ከ 13 ዓመታት ቆይታ በኋላ እ.ኤ.አ. ታህሳስ 31 ከስፍራው እንዲወጣ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት ወስኗል፡፡
12000 ወታደሮችን ያካተተው ጥምር ጦሩ ፣በአካባቢው በታጣቂዎች እና በሱዳን መንግሥት ጦር መካከል ከ2003 ጀምሮ በነበረው ግጭት የንጹኃንን እልቂት ለመከላከል ከ2007 ጀምሮ በዳርፉር ተሰማርቶ ቆይቷል፡፡