ሩሲያ ለ25 አመታት የሚቆይ በፖርት ሱዳን የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር ለመገንባት ከሀገሪቱ ጋር መስማማቷን አስታወቀች
የስምምነቱ ይዘትም በሩሲያ መንግስት ድረ ገጽ ላይ መውጣቱን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ጽፏል፡፡ የዚህ የጦር ሰፈር መገንባት ዋነኛ ዓላማም በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለማስጠበቅ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
ስምምነቱ በፈረንጆች ታህሳስ አንድ ቀን የተፈረመ ሲሆን እስከ 25 ዓመት እንደሚቆይና በየ 10 ዓመቱ እንደሚታደስ ተገልጿል፡፡ የባሕር ኃይሉ በአንድ ጊዜ እስከ አራት መርከቦች የሚያስተናግድ ሲሆን መርከቦቹ ደግሞ ኒዩክለር የታጠቁ ይሆናሉ ነው የተባለው፡፡ ይህ የጦር ሰፈር እስከ 300 በሚደርሱ ወታደራዊና ወታደራዊ ያልሆኑ ሰዎችም ይመራል ነው የተባለው፡፡
በስምምነቱ መሰረትም ሩሲያ የጦር መሳሪያዎችን፣ጥይቶችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን በሱዳን ወደቦችና አውሮፕላን ማረፊያዎች ማጓጓዝ ትችላለች፡፡በዚህ ጉዳይ ላይ ከሱዳን ባለሥለጣናት የተሰጠ አስተያየት እንደሌለ ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡ ሞስኮ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፊቷን ወደ አፍሪካ በማዞር ዓለም አቀፋዊ የበላይነትን ለመያዝ ማለሟን ጸሐፊዎች ያነሳሉ፡፡
እ.አ.አ በ2017 የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልባሽር በሞስኮ አድርገውት በነበረው ጉብኝት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ሀገሬን ከአሜሪካ ይጠብቁልኝ ማለታቸው ይታወሳል፡፡
በቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልባሽር የሥልጣን ዘመን ቱርክም በሰዋኪን ወደብ የጦር ሰፈር ለመገንባት ስምምነት አድርጋ እንደነበር ይታወሳል፡፡