ስለውቅያኖሶች የአለም ሙቀት ጋሻነት ምን ያህል ያውቃሉ?
ውቅያኖሶች በሰው ልጆች ከሚለቀቀው ካርበን ዳይ ኦክሳይድ 30 በመቶውን አምቀው ይይዛሉ
በኮፕ28 ጉባኤ ውቅያኖሶችን ለመጠበቅ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ይመከራል
28ኛው የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ28) ከሚመክርባቸው ጉዳዮች አንዱ የውቅያኖሶች ደህንነት ነው።
ባለፉት ሁለት አመታት ውቅያኖሶችን ለመጠበቅ በርካታ እርምጃዎች ተወስደዋል፤ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ያላቸው ድርሻ ላይም ግንዛቤው እያደገ ይገኛል።
ውቅያኖሶች ለሰው ልጆች ኦክስጂን ይመግባሉ፤ ከባቢ አየር እንዳይዛባም ትልቅ ድርሻ አላቸው።
ከምድራችን ስፋት ከሶስት አራተኛውን በላይ የሚሸፍኑት ውቅያኖሶች ከ50 እስከ 80 ፍጥረታትን ይይዛሉ።
እነዚህ ሰፊ ውሃማ አካላት የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ችግር በመቀነስ ረገድም ጉልህ አበርክቶ እንዳላቸው ነው የሚነገረው።
ውቅያኖሶች በግሪን ሃውስ ጋዞች ምክንያት ከሚለቀቅ ከመጠን ያለፈ ሙቀት 93 በመቶውን አምቀው ይይዛሉ።
የሰው ልጆች ከሚለቁት ካርበን ዳይ ኦክሳይድ ውስጥ 30 በመቶው በውቅያኖሶች የሚከማች መሆኑንም ተመራማሪዎች ይገልጻሉ።
ምድራችን ከሚያስፈልጋት ኦክስጂን ከ50 በመቶ በላዩ የሚገኘውም ከውቅያኖሶች ነው።
በየጊዜው አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የበካይ ጋዝ ልቀትና ተያያዥ ችግሮች ግን የውቅያኖሶችን የሰው ልጆች ጋሻነት እየተፈታተነ ነው።
የውቅያኖሶች ሙቀትና አሲዳማነት መጨመር በውስጡ የሚገኙ ፍጥረታት ህይወትን አደጋ ላይ ከመጣል አልፎ በቀጣይ ለሰው ልጆች ህልውናም አስጊ ሁኔታዎች እንደሚፈጥሩ ስጋቱ አይሏል።
ውቅያኖሶች የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው ጉዳት ገፈት ቀማሽ ቢሆኑም የመፍትሄውም ቁልፍ አካል ናቸው።
በዱባይ መካሄዱን የቀጠለው የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤም የሀገራት መንግስታት እነዚህን ግዙፍ ውሃማ ስፍራዎች እንዴት ከአደጋ እንጠብቅ በሚለው ዙሪያ ይመክራሉ።
በተለይም ሀገራት የአለም ሙቀት ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንዳይጨምር የገቡትን ቃል ተፈጻሚ በማድረግ የውሃማ አካላትን ደህንነት ማረጋገጥ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር ይደረጋል ተብሏል።