56 ከመቶ ውቅያኖሶች አረንጓዴ እየሆኑ ነው - ጥናት
ከምድራችን ጠቅላላ የየብስ ስፋት የሚልቀው ውሃማ ክፍል አረንጓዴ ቀለም እየያዘ መምጣቱን ተመራማሪዎች ተናግረዋል
የአየር ንብረት ለውጥ በውቅያኖስ ስነምህዳር ላይ ተጽዕኖው እየጎላ መሄዱ ተገልጿል
ከአለማችን ውቅያኖሶች ውስጥ 56 ከመቶው ቀለማቸው ወደ አረንጓዴነት መለወጡን አንድ ጥናት አመላከተ።
የአሜሪካ እና ብሪታንያ ተመራማሪዎች በኔቸር ጆርናል ላይ ያወጡት ጥናት እንደሚያሳየው የአየር ንብረት ለውጥ በውሃማ ክፍሎች ስነምህዳር ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እያየለ ነው።
አረንጓዴ እየሆነ ያለው የውቅያኖስ ክፍል ከጠቅላላው ደረቁ የምድር ክፍል የሚልቅ መሆኑንም ያነሳሉ።
ተመራማሪዎቹ ለውቅያኖሶች ቀለም ከሰማያዊነት ወደ አረንጓዴነት መቀየር በግልጽ ይህ ነው ምክንያቱ ብሎ ማስቀመጥ ቢቸገሩም የተስማሙባቸው ነጥቦች ግን አሉ።
የመጀመሪያው የሙቀት መጨመር በውቅያኖስ ውስጥ የሚኖሩ እጽዋትን ወደ ላይኛው የውቅያኖስ ክፍል እንዳይወጥ እያደረገ ነው የሚል ነው።
በውቅያኖሶች ውስጥ እጽዋት አረንጓዴ ቀለም እንዲኖራቸውና ምግባቸውን ከጸሃይ እንዲያገኙ የሚያደርገው (ክሎሮፋይል) መጠን በየአመቱ እየጨመረ መሄዱን ጥናቱ ያሳያል።
ይህ ለውጥ ግን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዘ ለመሆኑ እስከ 40 አመታት ሊወስድ የሚችል ጥልቅ ጥናትን ያሻል ነው የተባለው።
ከአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም (ናሳ) በሁለት አስርት አመታት ውስጥ ከህዋ ላይ ያነሳቸውን ምስሎች ተመርኩዞ የተደረገው ጥናት የአለም ሙቀት መጨመር ከውቅያኖሶች አረንጓዴ መሆን ጋር ያለውን ዝምድና ለመዳሰስ ቢሞክርም ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ግን ተቸግሯል።
ናሳ በቀጣዩ አመት የውቅያኖስ ስነምህዳርን ለማጥናት የምትውል ሳተላይት ያመጥቃል።
ከዚህች ሳተላይት የሚላኩ እጅግ ጥራት ያላቸው ምስሎችም ተመራማሪዎች በውቅያኖሶች ላይ የተጋረጠውን አደጋ መንስኤና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የሚጠቁም ጥናት እንዲያደርጉ ያግዛሉ ተብሏል።