ህዝቡ በተለያዩ ሚዲያዎች በሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮች ሳይደናገር አንድነቱን እንዲጠብቅ ኦነግ ጥሪ አቀረበ
ህዝቡ በተለያዩ ሚዲያዎች በሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮች ሳይደናገር አንድነቱን እንዲጠብቅ ኦነግ ጥሪ አቀረበ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ማእከላዊ ኮሚቴ በአንገብጋቢ ሀገራዊ፣ ክልላዊ እና የፓርቲው ጉዳዮች ላይ ላለፉት ሶስት ቀናት ውይይት ማድረጉን አስታውቋል፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ቀጄላ መርዳሳ የፓርቲውን የውይይት ነጥቦች እና የደረሰባቸውን ውሳኔዎች በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ከህዳሴ ግድቡ ውዝግብ ጋር በተያያዘ ላለፉት ስምንት ዓመታት ሲካሄድ የነበረው ድርድር አሁን በቅጽበት አቅጣጫውን ስቶ ግብጽና ኢትዮጵያን ውጥረት ውስጥ እያስገባ መሆኑን ፓርቲው ገልጿል፡፡
በአሜሪካ የተደረጉ ድርድሮች እና የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ጉዳይም ግልጽ አይደለም ያሉት አቶ ዳውድ እና ቀጄላ፣ የአባይ ጉዳይ የሁላችንም በመሆኑ በወንዙ እና በህዳሴ ግድቡ ላይ የሚደረጉ ድርድሮች እና ውሳኔዎች ሁላችንም ያገባናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የፓርቲው ማእከላዊ ኮሚቴም በግድቡ ዙሪያ የተፈጠሩ አለመግባባቶች በድርድር ብቻ መፈታት እንዳለባቸው ያምናል ያሉት የፓርቲው የበላይ አመራሮች፣ ኦነግ ከአባይ ጋር በተያያዘ የሚመጡ ማናቸውንም ጉዳዮች ከህዝብ ጋር በመሆን ለመጋፈጥ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ስለጥላቻ ንግግርም ማእከላዊ ኮሚቴው በአጽንኦት መወያየቱ ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮች ሊደናገር እንደማይገባ አመራሮቹ በመግለጫቸው አሳስበዋል፡፡ በተለያየ መልኩ ህዝብን ለመከፋፈል የሚደረጉ የጥላቻ ንግግሮች ሊቆሙ ይገባል ያለው ኦነግ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦችም በንግግሮቹ ሳይረበሹ የቆየ አንድነታቸውን ጠብቀው መቆም አለባቸው ብሏል፡፡
ከምርጫ ጋር በተያያዘ፣ ፓርቲው በክልል ደረጃ የተመሰረተው “ትብብር ለዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም” እንዲሁም በተዋረድ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተመሰረተው “ትብብር ለህብረ-ብሄር ዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም ጥምረት“ አካል በመሆን ለምርጫ እየተዘጋጀ ይገኛል ብለዋል አመራሮቹ በመግለጫቸው፡፡
ምርጫ ቦርድ የቀረቡለትን ሰነዶች ተመልክቶ ለጥምረቶቹ እውቅና እንዲሰጥ የጠየቀው ኦነግ ሙሉ አቅሙን በማስተባበር ለ ምርጫ 2012 ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ፣ እንዲሁም ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ በአመራሮቹ መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡
ፓርቲው ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋወር እንዲሁም በአባላቱና ደጋፊዎቹ ላይ በመንግስት ጫና እየተደረገ ነው ያሉት እነ አቶ ዳውድ መንግስት ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ጠይቀዋል፡፡
በምእራቡ የኦሮሚያ ክፍል የተዘጋው የስልክ ኔትዎርክ የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት የሚገድብ በመሆኑ ኔትዎርኩ መለቀቅ እንዳለበት እና የኮማንድ ፖስት እንቅስቃሴዎችም አስፈላጊው ክትትል ሊደረግባቸው እንደሚገባ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡