ሰኔ 14 ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝግ እንደሚሆኑ ጠ/ሚ ዐቢይ ገለፁ
በሶማሌ ክልል እና በሌሎች ክልሎች በሚገኙ 27 የምርጫ ክልሎች ምርጫው ጳጉሜ 1 ይካሄዳል
ምርጫ ጣቢዎች ማለዳ 12 ሰዓት ተከፍተው ምሽት 12 ሰዓት እንደሚዘጉ ተገልጿል
ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ የሰኔ 14 ሀገራዊ ምርጫን በማስመልከት በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልእክት “ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በዕለቱ ዝግ ይሆናሉ፤ እሱንም ለማካካስ ቀጥሎ በሚመጣው ቅዳሜ ወደ ስራ የምንገባ ይሆናል” ብለዋል፡፡
“ሰኔ 14፣ 2013 ሁለት ነገር እንትከል። በካርዳችን ዴሞክራሲን፣ በእጃችን ችግኞችን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኔ 14 ድምጽ ለመስጠት መረጩ ሕብረተሰብ በነቂስ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በግንቦት ወር ሊካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም አስፈላጊ የምርጫ ቁሳቁሶች በተያዘላቸው ጊዜ ተዘጋጅተው ባለመጠናቀቃቸው በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲካሄድ ተወስኗል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሶማሌ ክልልን ጨምሮ በ27 የምርጫ ክልሎች ሰኔ 14 ምርጫው እንደማይካሄድ አስታውቋል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የሶማሌ ክልል እንዲሁም የምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልነት ሕዝበ ውሳኔን ጨምሮ በ27 የምርጫ ክልሎች ምርጫው ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሚካሄድ ባለፈው ሳምንት መግለጻቸው ይታወሳል።
ምርጫ ጣቢዎች ማለዳ 12 ሰዓት ተከፍተው ምሽት 12 ሰዓት እንደሚዘጉ የቦርዱ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ ሶልያና ሽመልስ በትላንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ አስገንዝበዋል።
በመጪው ሰኞ ለሚካሄደው የድምጽ መስጠት ተግባር አገልግሎት ላይ የሚውሉ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ወደ ተለያዩ የምርጫ ክልሎች እየተላኩ መሆኑንም ሶልያና ሽመልስ ገልፀዋል።