“ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት ከጀመርን ዓመት አልፎናል”- ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
በምርጫው ማግስት የሚያጋጥሙ ችግሮች ካሉ ለችግሮቹ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የሰው ኃይልና የቁሳቁስ ዝግጅት ማድረጉንም ነው የገለጸው
ኮሚሽኑ ምርጫውን በሰላም ለማጠናቀቅ የሚያስችል ሙሉ ዝግጁነት እንዳለው አስታውቋል
አገር አቀፉን ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ዝግጁ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ከምርጫ ውጤት ይፋ መሆን ጋር ተያይዞ የጸጥታ ችግር ይከሰታል የሚል ዕምነት እንደሌለው ኮሚሽኑ ገልጿል።
እስካሁን ባለው የምርጫ እንቅስቃሴ 58 የምርመራ መዝገቦች ማደራጀቱን ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።
6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ የፊታችን ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚካሄድ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል።
ምርጫ በመጣ ቁጥር የጸጥታ ሁኔታው ችግር በመሆኑ ምን እየሰራችሁ ነው ሲል አል ዐይን አማርኛ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን ጠይቋል።
ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ኮሚሽኑ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን ዝግጅት ከጀመረ አንድ ዓመት አልፎታል ብለዋል።
ምርጫው ከማንኛውን የደህንነት ስጋት ነጻ እንዲሆን ሰባት ንዑስ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ ገብቷል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭት፣ የምርጫ ጣቢያዎች፣ የምርጫ ወንጀል ክትትል ኮሚቴዎች እና ሌሎች አደረጃጀቶች ተደራጅተው ስራ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እስካሁን ከምርጫ ጋር በተያያዘ የፖስተር መቅደድ፤ እጩዎችን ማስፈራራት፤ የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭቶችን ማወክ እና ሌሎች ተያያዥ ወንጀሎች መፈጸማቸውንም ተናግረዋል።
ይህ የምርጫ ምርመራ ቡድን ከክልሎች እና ከተማ አስተዳድሮች ፖሊስ ኮሚሽኖች ጋር በመነጋገር በውይይት የሚፈታውን በውይይት ምርመራ የሚጠይቁትን ደግሞ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል እና በመመርመር በህግ እንዲጠየቁ በማድረግ ላይ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ ነግረውናል።
የምርጫ ምርመራ ቡድኑ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ 58 የምርመራ መዝገቦችን በማደራጀት ለጠቅላይ አቃቢ ህግ የተላከ ሲሆን 36ቱ መዝገቦች በፍርድ ቤት ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል ብለዋል።
በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ሀይሎች ምርጫውን እንዳያስተጓጉሉ ምን ዝግጀት ተደርጓል? የሚል ጥያቄ ከአል ዐይን የቀረበላቸው ምክትል ኮሚሽነሩ “ስጋቱ ባለባቸው ቦታዎች ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እርምጃ እየወሰደ እና ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማድረግ ላይ ነው” ሲሉ መልሰዋል።
ፌደራል ፖሊስ ከምርጫ ውጤት ጋር በተያያዘ ነጻ እና ገለልተኛ በሆነ መንገድ ህግ የማስከበር ስራውን ብቻ እንደሚያከናውንም ኮሚሽነር ዘላለም ተናግረዋል።
ከምርጫ ውጤት ይፋ መሆን ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮች ቢፈጠሩ ዝግጅታችሁ ምን ይመስላል? በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄም “ምርጫ ቦርድ አጠቃላይ የምርጫ ውጤቱን ይፋ ካደረገ በኋላ የጸጥታ ችግር ይከሰታል ብለን አንጠብቅም፤ የሚፈጠሩ ችግሮች ካሉ ግን የሰው ሃይል እና ለጸጥታ ማስከበር ስራ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን አድርገናል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።