ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ውጭ በተከፈቱ 79 የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ በሕገ ወጥ መንገድ መካሔዱን ቦርዱ ገለፀ
ሕገ ወጥ የምርጫ ጣቢያዎች የተከፈቱት በደቡብ ክልል፣ በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳድሮች ነው
ቦርዱ ከሶማሌ ክልል በተጨማሪ የመራጮች ድምጽ ድምጽ ጳጉሜ 1 የሚሰጥባቸውን ስፍራዎችም አስታውቋል
በእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች የተመዘገቡ መራጮች ከምርጫ ቦርድ እውቅና ውጪ የተካሄዱ በመሆናቸው ውድቅ ተደርገዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 02 ቀን 2013 ዓ.ም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር ካከናወነ በኋላ ባደረገው ስብሰባ ከ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ ጋር የተያያዙ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችን ይፋ አድርጓል።
ቦርዱ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከቦርዱ እውቀውና ውጭ የተከፈቱ 2፣ በድሬደዋ ከተማ መስተዳድር ከቦርዱ እውቅና ውጭ የተከፈቱ 6 እንዲሁም በደቡብ ክልል ከቦርዱ እውቅና ውጭ የተከፈቱ 71፣ በድምሩ 79 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተደረጉ የመራጮች ምዝገባዎች ህጋዊ አይደሉም ሲል ቦርዱ ወስኗል። የተመዘገቡ መራጮችን ድምፅ አሰጣጥ ሂደት አስመልክቶ ቦርዱ ከድምጽ አሰጣጥ ቀን በፊት ውሳኔ እንደሚሰጥ ገልጿል፡፡
አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመራጮች ምዝገባን የተረጋገጠ ቁጥር የማጣራት ሂደቱን ያጠናቀቀ ሲሆን ለ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 37 ነጥብ 4 ሚልዮን መሆኑን ገልጿል።
ይህ ቁጥር በሶማሌ ክልል በምርመራ የተነሳ የመራጮች ምዝገባ የታገደባቸው 14 ምርጫ ክልሎችን አንደማይጨምርም ቦርዱ አስታውቋል።
በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ድምጽ መስጠት የማይቻልባቸው እና በምትኩ ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ምርጫ የሚደረግባቸውን ስፍራዎችም ቦርዱ አስከምጧል፡፡
እነዚህም፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል-መተከል፣ ሺናሻ ልዩ፣ ካማሽ እና ዳለቲ
በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ቤጊ፣ ሰኞ ገበያ፣ አያና፣ገሊላ፣አሊቦ፣ጊዳሚ፣ ኮምቦልቻ
በአማራ ክልል ደግሞ ማጀቴ (ማኮይ)፣ አርጎባ ልዩ፣ ሸዋሮቢት፣ ኤፌሶን፣ ጭልጋ 1፣ ጭልጋ 2፣ ላይ አርማጭ፣ አንኮበር
ደቡብ ክልል ደግሞ ሱርማ ልዩ ፣ ዲዚ ልዩ፣ ቀይ አፈር መደበኛ፣ ማጀት መደበኛ፣ ሸኮ ልዩ፣ ቴፒ እንዲሁም
በሐረሪ ክልል ጀጎል ልዩ ፣ ጀጎል መደበኛ ናቸው፡፡
በፀጥታ ችግሮች የተነሳ ድምጽ አሰጣጥ በዚህ ቀን በሚከናውንባቸው ስፍራዎች የጸጥታውን ሁኔታ የማሻሻል ኃላፊነት ያለባቸው የመንግስት ፀጥታ አካላት ለዚሁ ዝግጅት እንዲያደርጉም ቦርዱ አሳስቧል።
ምርጫ ቦርድ ከዚህ በፊት 54 የምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ችግሮች ያጋጠሙ መሆናቸውን መግለጹ ይታወሳል።
ቦርዱ ከፓርቲዎች ጋር ምክክር ካደረገ በኋላ ጷግሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ድምጽ የሚሰጥባቸው የክልል እና የተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ክልሎችን ቁጥር ወደ 27 ዝቅ እንዲል ማድረጉን ገልጿል።
በሶማሌ ክልል የሚደረገው ድምጽ አሰጣጥ እና የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ በጳጉሜ 01 ቀን 2013 እንዲደረግ መወሰኑ ይታወሳል።