በእየሩሳሌም በተፈጸሙ ሁለት ፍንዳታዎች አንድ ሰው ሲሞት 18 ቆስለዋል
ከተጎዱት መካከል ሁለቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ ናቸው ተብሏል
የእስራኤል ፖሊስ፤ ፍንዳታዎቹ በፍልስጤም በኩል የተፈጸሙ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግሯል
በእየሩሳሌም ከተማ ላይ በተፈጸሙ ሁለት የተለያዩ ፍንዳታዎች አንድ ሰው ሲሞት 18 ሰዎች መቁሰላቸው የእስራኤል ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡
ረቡዕ ጠዋት በኢየሩሳሌም ማዕከላዊ አውቶቡስ ጣቢያ አጠገብ በደረሰ ፍንዳታ ከቆሰሉት መካከል ቢያንስ ሁለቱ በከባድ ሁኔታ ላይ መሆናቸውንም ነው ዘ ጀሩሳሌም ፖስት ጋዜጣ ባለስልጣናቱን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ከተጎዱት መካከል ሁለቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ጋዜጣው አክሎ ገልጿል።
የመጀመሪያው ፍንዳታ የተከሰተው በጂቫት ሻውል የኢየሩሳሌም ዋና መግቢያ አቅራቢያ ነው፣ ከቀኑ 7 ሰዓት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከቀኑ 7፡30 ላይ በራሞት መጋጠሚያ ወደ እየሩሳሌም ሌላ መግቢያ ላይ ነበር፡፡
ከፍንዳታዎቹ በኋላ ተጎጂዎቹ በከተማው ወደሚገኙ ሻሬ ዘዴቅ እና ሃዳሳ አይን ከረም ሆስፒታሎች መወሰዳቸውንም ተገልጿል፡፡
የዕብራይስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ እንደሚያመለክተው ከሆነ ፍንዳታዎቹ የተፈጠሩት በከረጢት ውስጥ በተቀመጠ ፈንጂ እንደሆነ ይገመታል፡፡
የእስራኤል ፖሊስ ፍንዳታዎቹ በፍልስጤም በኩል የተፈጸሙ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግሯል፡፡
ፖሊስ በምክንያትነት የሚያስቀምጠውም ፍንዳታዎቹ የተከሰቱት የፍልስጤም ባለስልጣናት የ16 አመት ፍለስጤማዊ ልጅ በእስራኤል ወታደሮች እንደተገደለ ከተናገሩ በኋላ መሆኑ ነው፡፡