እስራኤል በዌስትባንክ ሁለት የሮቦት ወታደሮችን ማሰማራቷ ተገለጸ
አመፅ ሲነሳ አስለቃሽ ጭስ እና የፕላስቲክ ጥይት ይተኩሳሉ የተባሉት ሮቦቶች የወታደሮችን ህይወት እንደሚታደጉ ተገልጿል
ፍልስጤማውያን ግን ሮቦቶቹ በንፁሃን ላይ ሊሞከሩ አይገባም፤ ለመረጃ ጠላፊዎች ከተጋለጡም እልቂት ሊያስከትሉ ይችላሉ እያሉ ነው
እስራኤል ተቃውሞ በሚበዛበት ዌስትባንክ ሁለት የተለያዩ አካባቢዎች የሮቦት ወታደሮችን ማሰማራተ ተነገረ።
አመፅ ሲነሳ አስለቃሽ ጭስ ይለቃሉ የተባሉት ሮቦቶች የወታደሮችን ህይወት እንደሚታደጉ ተገልጿል።
ፍልስጤማውያን ግን ሮቦቶቹ በንፁሃን ላይ ሊሞከሩ አይገባም፤ ለመረጃ ጠላፊዎች ከተጋለጡም እልቂት ሊያስከትሉ ይችላሉ እያሉ ነው።
አል አሩብ በተሰኘው የፍልስጤማውያን የስደተኞች ካምፕ እና በዌስትባንክ መሀል ከተማ የተተከሉት ሮቦቶች፥ ለአመፅ የወጡ ሰዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ እና ለከፋ ጉዳት የማይጥሉ የፕላስቲክ ጥይቶችን ይተኩሳሉ ተብሏል።
ሮቦቶቹ ወታደሮች ኢላማቸውን ለማግኘት ሰው ሰራሽ አስተውሎት ይጠቀማሉ። ዙሪያ ገባቸውን ተዘዋውረው የሚመለከቱባቸው ሌንሶች የተገጠመላቸው ሲሆን፥ አስለቃሽ ጭስና የፕላስቲክ ጥይት መተኮሻ እጅም አላቸው።
ዋነኛ አላማቸውም የእስራኤልንም ሆነ የፍልስጤም ወታደሮች ህይወት መታደግ ስለመሆኑ የእስራኤል ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የቤንያሚን ኔታንያሁ ዳግም መመረጥን ተከትሎ በዌስትባንክ ተቃውሞው በበረታበት ወቅት እየተሞከሩ ስለሚገኙት ሮቦቶች የፍልስጤማውያን ምልከታ ግን ተቃራኒ ነው።
በአል አሮብ ስደተኛ ጣቢያ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን፥ ሮቦቶቹ ከወታደርም ፈጣን ናቸው ያለምንም የማስጠንቀቂያ ድምፅ ይተኩሳሉ።፤ በጭስም ያፍኑናል የሚል ቅሬታ አላቸው።
"የእስራኤል የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መለማመጃ አይደለንም፤ ማሽኖቹን የሚቆጣጠር ሰው ስለሌለም ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ" የሚሉ ትችቶቾን ፍልስጤማውያን እያነሱ መሆኑን አሶሼትድ ፕረስ አስነብቧል።
ከወር በፊትም የእስራኤል ጦር ከፍልስጤማውያን ጋር በሚጋጭባት ሄብሮን ከተማ መሰል ሮቦቶች ተተክለዋል ነው የተባለው።
የሀገሪቱ መንግስት ግን ከዌስትባንክ ውጭ ሮቦቶቹን ጥቅም ላይ ስለማዋሉ ያለው ነገር የለም።
የእሳት አደጋን ለመቆጣጠር የሚውሉ ስርአቶችን ለአሜሪካ ጭምር የሚያቀርበው ስማርት ሹተር የተሰኘ ኩባንያ ነው ሮቦቶቹን የሰራው።
የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚቻል ሞር፥ ሮቦቶቹ ለመተኮስ በሰው መታዘዝ አለባቸው፤ ከርቀት በሪሞት መታዘዛቸው የወታደሮችን ህይወት ለመታደግ በማለም ነው ብለዋል።
ፍልስጤማውያኑ ስጋት ሊገባቸው እንደማይገባ ነው ያሳሰቡት።
እስራኤል አሁን ላይ እየሞከርኩት ነው ያለችውን ቴክኖሎጂ አሜሪካ በኢራቅ፣ ደቡብ ኮሪያ ደግሞ ከጎረቤቷ ሰሜን ኮሪያ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ተጠቅመውበታል።