በኔታንያሁ የሚመራው ጥምር የፖለቲካ ፓርቲ ከ120 የፓርላማ መቀመጫ 64ቱን ማግኘት ችሏል
በእስራኤል በተካሄደ ጠቅላላ ምርጫ በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያን ኔታንያሁ የሚመራው ጥምር ፓርቲ ማሸነፉ ተገለጸ።
በዚህም ቀኝ ዘመሙ የፖለቲካ ፓርቲ ከ120 የእስራዔል ክኔስት (ፓርላማ) መቀመጫ አብዛኛውን ማግኘት የቻለ ሲሆን፤ በእስራዔል ፖለቲካ ውስጥ ታዋቂ የሆኑት ቤንያን ኔታንያሁ ወደ ፖለቲካው መመለስ የቻለ ሆኗል።
በትናትናው እለት ይፋ በተደረገው የእስራዔል ምርጫ ውጤት በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያን ኔታንያሁ የሚመራው ጥምር ፓርቲ ከ120 የእስራዔል ክኔስት (ፓርላማ) መቀመጫ 64 መቀመጫዎችን ማሸነፉ ተገልጿል።
ከ64ቱ መቀመጫዎች ውስጥ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያን ኔታንያሁ ፓርቲ የሆነው ሊኩዊድ 32 መቀመጫዎችን ማግኘት መቻሉም ነው የተገለፀው።
በዚህ ምርጫ አብላጫ የምክር ቤት ወንበር ያገኙት ሊኩድ ፓርቲ እና ቀኝ አክራሪ የእስራኤል ፓርቲዎች በጋራ አዲስ መንግሥት እንደሚመሰርቱ ይጠበቃልም ተብሏል።
ቤንያሚን ኔታንያሁ የምርጫ ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት "የእስራኤላዊያንን እምነት ማግኘት ችለናል፣ የተረጋጋ መንግስትም እንመሰርታለን" ብለዋል።
የምርጫው የመጨረሻ ውጤት ለህዝብ ይፋ መደረጉን ተከትሎም ቤንያሚን ኔታንያሁ ዳግም ወደ ስልጣን እንደሚመጡ ይጠበቃል።
የቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ዳግም ወደ ስልጣን ከተመለሱ በሀገሪቱ አቃቤ ህግ ለተመሰረተባቸው የሙስና ክስ እልባት ሊሰጥበት እንደሚችልም ተገልጿል።
በእስራኤል የፖለቲካ አለመረጋጋት ከተከሰት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ አምስተኛዋን ምርጫ አካሂዳለች።