የቀድሞ ዋን ዳይሬክሽን የሙዚቃ ቡድን አባል ሊያም ፔይን ከሆቴል ህንጻ ላይ ወድቆ ህይወቱ አለፈ
የ31 አመቱ ሊያም ፔይን ከመሞቱ በፊት ከፍተኛ መጠን ያለው በአደንዛዥ ዕፅ እና በአልኮል ወስዶ እንደነበር ተነግሯል
ድምጻዊው በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት ወዲያው ህይወቱ ያለፈ ሲሆን ፖሊስ በአሁኑ ሰአት የአስከሬን ምርመራ እያደረገ ይገኛል
የቀድሞ ዋን ዳይሬክሽን የሙዚቃ ባንድ አባል የነበረው ሊያም ፔይን እሮብ እለት በአርጄንቲና ቦነስ አይረስ ከሆቴል ክፍል በረንዳ ላይ ወድቆ ሞቶ ተገኝቷል ሲል የአካባቢው ፖሊስ ገልጿል።
የ31 አመቱ እንግሊዛዊ የፖፕ ሙዚቃ ኮከብ ለእረፍት በነበረበት የፓሌርሞ ሰፈር በሚገኘው የካሳ ሱር ሆቴል ሶስተኛ ፎቅ ላይ መውደቁን ተከትሎ ባጋጠመው ከፍተኛ ጉዳት ወዲያው ህይወቱ አልፏል።
ፖሊስ ድምጻዊው ከመሞቱ ቀደም ብሎ በአልኮል እና ዕጽ ተጽዕኖ ውስጥ የሚገኝ ሰው ሆቴሉን እየረበሸ እንደሚገኝ የሆቴሉ ስራአስኪያጅ ለፖሊስ ጥሪ አድርጎ እንደነበር ተነግሯል።
የአካባቢው የድንገተኛ ህክምና ክፍል ኃላፊ አልቤርቶ ክሬሰንቲ የፎረንሲክ ባለሙያዎች የአሟሟቱን ሁኔታ እና የአስከሬን ምርመራ እያደረጉ ነው ብለዋል።
የሊያም ሞት ከመሰማቱ ከ45 ደቂቃ በፊት ድምጻዊው በመዋኛ ገንዳ አካባቢ ከወገቡ በላይ እርቃኑን ሆኖ ተንቀሳቃሽ ምስል አጋርቶ ነበር።
በ2010 በብሪታንያ ኤክስ ፋክተር የሙዚቃ ተሰጥኦ ውድድር ላይ ብቅ ያሉት 5 ታዳጊዎች ከውድድሩ በኋላ የመሰረቱት ዋን ዳይሬክሽን የተሰኝው ባንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቶ ነበር።
ሄሪ ስታይል ፣ ዛያን ማሊክ ፣ ኒያል ሆራን ፣ ሉዊስ ቶሚሊንሰን እና ሊያም ፔይን በ2016 ለመለያየት ከመወሰናቸው በፊት ለ6 አመታት በነበራቸው ቆይታ አልበም እና ነጠላዜማዎችን በመስራት እንዲሁም በተለያዩ የአለም ክፍሎች ባዘጋጇቸው ኮንሰርቶች ተወዳጅነትን አትርፈዋል።
በ2019 ኤል ፒ 1 የተሰኝውን የመጀመርያ አልበሙን ለአድማጭ ያደረሰው ሟቹ ሊያም ፔይን በ2023 በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ሁለተኛ አልበሙን ለመልቀቅ ዝግጅቱን ስለመጨረሱ ተናግሮ ነበር።