የኡራጋይ ብሄራዊ ቡድን ተከላካይ ሁዋን ኢዝኪየርዶ በሜዳ ውስጥ ባጋጠመው አደጋ ህይወቱ አለፈ
ተጨዋቹ በ84ኛው ደቂቃ ከማንም ሰው ጋር ንክኪ ሳይኖረው በሜዳ ውስጥ ሲወድቅ ታይቷል
የ27 አመቱ ወጣት በሜዳ ውስጥ ራሱን ስቶ ከወደቀ በኋላ አዕምሮው ሙሉ ለሙሉ ስራ በማቆሙ ህይወቱ አልፏል
የኡራጋይ ብሄራዊ ቡድን ተከላካይ ሁዋን ኢዝኪየርዶ በሜዳ ውስጥ ራሱን ስቶ ከወደቀ ከስድስት ቀናት በኋላ ህይወቱ ማለፉ ተሰምቷል፡፡
በብራዚል አዘጋጅነት እየተካሄደ በሚገኝው የ2024ቱ “ኮፓ ሊበረታዶረስ” ግጥሚያ ላይ ክለቡ ናሲዮናል ከሳኦፖሎ የእግርኳስ ቡድን ጋር እየተጫወተ ባለበት በ84ኛው ደቂቃ ከማንም ሰው ጋር ንክኪ ሳይኖረው በሜዳ ውስጥ ሲወድቅ ታይቷል፡፡
ተጫዋቹ በሳኦፖሎ በሚገኝው አልበርት አንስታይን ሆስፒታል ጽኑ ህክምና ክፍል ውስጥ ህክምናውን ሲከታተል ቆይቶ በዛሬው እለት ህይወቱ ማለፉ ነው የተነገረው፡፡
የሆስፒታሉ ሃኪሞች ሁዋን የሞተበት ምክንያት የአዕምሮ መስራት ማቆም (ብሬን ዴዝ) እንደሆነ የገለጹ ሲሆን የአእምሮውን ስራ ማቆም ተከትሎ ሳንባ እና ልቡ ተገቢውን ስራ ለማከናወን በመቸገራቸው በማሽን ሲረዳ እንደቆየ ተናግረዋል፡፡
“ብሬን ዴዝ” በግርድፍ ትርጉሙ “የአእምሮ መሞት” በመባል የሚታወቀው ገዳይ በሽታ መተንፈስ ፣ የልብ ምት እና የደም ዝውውርን የሚያሳልጠው የአዕምሮ ክፍል ስራ ሲያቆም የሚከሰት እንደሆነ ይነገራል፡፡
ይህ አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች የተወሰኑ ጊዜያትን በማሽን ድጋፍ ህይወታቸው ሊቀጥል ቢችልም በፍጹም ማገግም አይችሉም፡፡
ሞቱን ተከትሎ የኡራጋዩ ክለብ ናስዮናል በይፋዊ የኤክስ (ትዊተር) ገጹ “ተወዳጁን የቡድናችንን አባል ሁዋን ኢዝኪየርዶ ከዚህ አለም ማለፉን ስንገልጽ በታላቅ ሀዘን ውስጥ ሆነን ነው” ሲል ሞቱን ይፋ አድርጓል፡፡
አክሎም የማይተካ አጋራችንን ነው ያጣናው ለቤተሰቦቹ ለወዳጆቹ እና ለቡድን አጋሮቹ መጽናናትን እንመኛለን ብሏል፡፡
የኡራጋይ እግር ኳስ ፌደሬሽን በተመሳሳይ ሀዘኑን የገለጸ ሲሆን የአርጄንቲና ፣ ኮሎምቢያ ፔሩ እና ፓራጓይ የእግርኳስ ፌደሬሽኖች ለሁዋን ክለብ እና ቤተሰቦቹ በሞቱ የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል፡፡
የብራዚል እግር ኳስ ፌደሬሽን በበኩሉ በዛሬው እለት በሚከናወኑ ቀሪ “የኮፓ ሊበረታዶረስ” ጨዋታዎች ላይ ለተጫዋቹ የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት እንዲደረግ አዟል፡፡
“ኮፓ ሊበረታዶረስ” በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1960 ጀምሮ በደቡብ አሜሪካ እግር ኳስ ቡድኖች መካከል የሚደረግ አመታዊ ውድድር ሲሆን የዚህ አመት አዘጋጅ ብራዚል ነች፡፡
በደቡብ አሜሪካ የሚገኙ 32 ክለቦች በሚሳተፉበት በዚህ አህጉራዊ ውድድር አርጄንቲና እና ብራዚል በርካታ ክለቦችን በማሳተፍ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡