የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ተከታይ “ኤጂአይ” ምንድን ነው?
ኦፕንኤአይ “ጂፒቲ - 4”ን የሚተካና የሰው ልጆች የሚከውኑትን ማንኛውም ስራ የሚሰራ ቴክኖሎጂ ማሰልጠን መጀመሩን አስታውቋል
አዲሱ ሞዴል በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የተጀመረውን ፉክክር ከፍ እንደሚያደርገው ይጠበቃል
የአሜሪካው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኩባንያ “ኦፕንኤአይ” አዲስ የኤአይ ሞዴል ማሰልጠን መጀመሩን ይፋ አደረገ።
ኩባንያው በድረገጹ በለቀቀው መገለጫ አዲሱ ሞዴል ለምን ያህል ጊዜ እንደሚሰለጥን እና ስያሜው ምን እንደሚሆን ግን አልገለጸም።
ይሁን እንጂ ቴክኖሎጂው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ወደ “አርቲፊሻል ጀነራል ኢንተለጀንስ” ወይም “ኤጂአይ” ከፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
“ጂፒቲ-4”ን ይተካል ተብሎ የሚጠበቀው የኦፕንኤአይ “አይጂኤ” እንደ ሰው ልጆች አዕምሮ ማሰብና የሰው ልጅ የሚከውናቸውን ነገሮች ሁሉ መስራት የሚችል መሆኑ ይነገራል።
“ጂፒቲ -5” የሚል ስያሜ ይሰጠዋል ተብሎ የሚጠበቀውና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስን አንድ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርግ የታመነበት “ኤጂአይ” ከጂፒቲ -4 እና ቻትጂፒቲ የተሻሉ ስራዎችን መከወን እንደሚችል ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።
ኮምፒውተር ከሰው ልጅ አዕምሮ ጋር የሚስተካከል አቅም ሊኖረው አይችልም የሚለው ጉዳይ አከራካሪ ቢሆንም የኦፕንኤአይ ያስጀመረው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አቢዮት ተአምር ሊያሳይ እንደሚችል የበርካቶች ግምት ነው።
ተቀመጭነቱን ሳንፍራንሲስኮ ያደረገው ኦፕንኤአይ ከሜታው “ላማ -3”፣ ከጎግል “ጂሚኒ” እና ከአንትሮፒኩ “ክላውድ -3” ከፍተኛ ፉክክር እየገጠመው ይገኛል።
ኩባንያው በቅርቡም እንደ አማዞን አሌክሳ እና እንደ አፕሏ ሲሪ በድምጽ እገዛ ለማግኘት የሚያስችለው የጂፒቲ 4 ማሻሻያ “ጂፒቲ -40” ማስተዋወቁ ይታወሳል።
የበርካቶችን ስራ ያቀለለው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስራቸውን የነጠቃቸው ሰዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፤ ወደፊት የደቀነው አደጋም የበርካቶች ስጋት ነው።
በምርጫ ወቅት የተዛቡ መረጃዎችን ለማጋራት እየዋለ ነው፤ የቅጂ መብትንም እየጣሰ ይገኛል የሚሉ ክሶችም በብዛት እየቀረቡበት ነው።
ክሱ የበዛበት የጂፒቲ - 4 ፈጣሪ ኩባንያ ኦፕንኤአይ ዋና ስራ አስፈጻሚውን ሳም አልትማን ያካተተና በ90 ቀናት ውስጥ የቴክኖሎጂውን ስጋትና እድል ገምግሞ ምክረሃሳብ የሚያቀርብ ኮሚቴ ማደራጀቱን በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል።