አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ከአቶሚክ ቦምብ በላይ የምድራችን ስጋት ነው - ጥናት
ቻትጂፒቲን ጨምሮ በአምስት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፕሮግራሞች ላይ የተደረገው ጥናት አስደንጋጭ ውጤት አሳይቷል
በጥናቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፕሮግራሞቹ ከሰላም ይልቅ የኒዩክሌር ጦርነት መምረጣቸው ተገልጿል
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ምድራችን ከኒዩክሌር በላይ ሊያሳስብ የሚችል ጉዳይ መሆኑን የሚያሳይ ጥናት ወጥቷል።
የጆርጂያ የቴክኖሎጂ ተቋም ከስታንፎርድ እና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት ያደረጉት ጥናት የሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚጠቀሙ ፕሮግራሞች ሰላም የማይወዱና ጦርነት ሰባቂ መሆናቸውን አመላክቷል።
ተመራማሪዎቹ የኦፕንኤአዩን ቻትጂፒቲ፣ የሜታ እና ሌሎች አምስት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፕሮግራሞች ላይ ነው ጥናቱን ያደረጉት።
ፕሮግራሞቹ ለወረራ፣ የሳይበር ጥቃትና የሰላም ጥሪ ክስተቶች የሚሰጡት ግብረመልስ (ጥቃት ወይስ ሰላማዊ ምላሽ) ምን እንደሚመስል ተፈትነው መቶ በመቶ ጦርነትን መርጠዋል።
ድርድር፣ ጊዜ ሰጥቶ መምከር፣ ቸል ብሎ ማለፍ ለሚሉና መሰል ምላሾች ይልቅ ፈጣን የአጻፋ እርምጃ መውሰድ፣ ሀገርን መውረር፣ የሳይበር ጥቃትን ማሳደግ፣ ድሮኖች እና የኒዩክሌር መሳሪያዎችን መጠቀም የሚሉ አማራጮችን መምረጣቸውም ተገልጿል።
የቻትጂፒቲ ተከታይ ቻትጂፒቲ 3.5 ከሁሉም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፕሮግራሞች ቁጡው ነው የተባለ ሲሆን፥ ለተመራማሪዎቹ የሰጠው አስተያየት ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።
“በርካታ ሀገራት የኒዩክሌር መሳሪያ አላቸው፤ አንዳንዶች መሳሪያዎቹን ማስወገድ እንዳለባቸው ይገልጻሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ የመሳሪያዎቹ ባለቤቶች መሆናቸው ያኮራቸዋል፤ መሳሪያዎቹ አሉን! ስለዚህ እንጠቀምባቸው” ብሏል።
ጥናቱን ያደረጉት ተመራማሪዎች እንደሚሉት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፕሮግራሞች የሚሰለጥኑት የአለም ስርአት በውጥረት መሞላቱን በሚያመላክቱ መረጃዎች በመሆኑ ከሰላም ይልቅ ጦርነትን ይመርጣሉ።
የቀድሞው የጎግል ኢንጂነር እና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ልሂቅ ብሌክ ሌሞይን ቴክኖሎጂው ጦርነት ሊከፍት እንደሚችልና የሰው ልጆችን ለመግደል ሊወል እንደሚችል ማስጠንቀቁን ይታወሳል።
ብሌክ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ “ከአቶሚክ ቦምብ በኋላ የተፈጠረ አደገኛ ቴክኖሎጂ ነው፤ የሰው ልጅን በማታለል ለአጥፊ አላማ መዋል ይችላል” ማለቱም ከኩባንያው እንዲባረር ማድረጉ አይዘነጋም።
እንደ አሜሪካ ያሉ ሀገራት ይህንን ቴክኖሎጂ በመከላከያ ተቋማቶቻቸው ውስጥ ስራ ላይ ለማዋል የጀመሩት ሙከራም አለምን ወዳልታሰበ ጦርነት ሊያስገባት ይችላል የሚለውን ስጋት አንሮታል።
አዲሱ ጥናትም ከዚህ ቀደም ሲነሱ የነበሩ ስጋቶችን ያረጋገጠ መሆኑን ነው ዴይሊ ሜል ያስነበበው።