ትራምፕ ምርጫውን ካሸነፉ ወዲያውኑ ሩሲያ እና ዩክሬንን ወደማደራደር መግባት እንደሚፈልጉ ኦርባን ተናገሩ
ኦርባን የአውሮፓ ሀገራት ለዩክሬን የሚያደርጉትን ወታደራዊ ድጋፍ ሌሎች አጋሮቿ ከሚያደርጉት ጋር በማነጻጸር ጠንካራ ትችት በማቅረብ ይታወቃሉ
አርባን ትራምፕ ዩክሬን እና ሩሲያን ማደራደር እንደሚፈልጉ ለአውሮፓ መሪዎች የተናገሩት በዋሽንግተን ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ነው
ትራምፕ ምርጫውን ካሸነፉ ወዲያውኑ ሩሲያ እና ዩክሬንን ወደማደራደር እንደሚገቡ ኦርባን ለአውሮፓ ህብረት በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል።
የሪፐብሊካኑ እጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በመጭው ህዳር የሚካሄደውን ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ ሩሲያ እና ዩክሬንን ወዲያውኑ ወደማደራደር እንደሚገቡ የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክተር ኦርባን በጽሁፍ ለአውሮፓ መሪዎች ነግረዋቸዋል ተብሏል።
ለአውሮፓ ህብረት ካውንስል ምክርቤት ፕሬዝደንት ቻርለስ ሚሸል እና ለሁሉም መሪዎች የተጋራው ይህ ደብዳቤ የተጻፈው፣ ኦርባን ከትራምፕ ጋር ካወሩ እና እንዲሁም ዩክሬንን፣ ሩሲያን እና ቻይናን ከጎበኙ በኋላ ነው።
"እኔ ማረጋገጥ የምትችለው፣ ትራምፕ የማደራደር ስራውን ለመጀመር በዓሉ ሲመታቸው እስከሚካሄድ እንደማይጠብቁ አረጋግጣለሁ። ለዚህ ዝርዝር እና ጥሩ እቅድ አላቸው" ሲሉ ኦርባን ጽፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኦርባን ሀንጋሪ የአውሮፓ ህብረት ምክርቤት ፕሬዝደንትነትን ከተረከበች በኋላ ወደ ሞስኮ በማቅናት የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረበት ከፈረንጆቹ የካቲት 2022 ወዲህ የጀመሪያው የአውሮፓ መሪ ሆነዋል።
ኦርባን የሞስኮ ጉብኝታቸውን "የሰላም ተልእኮ" ሲሉ ነበር የገለጹት።
ነገርግን የኦርባን ጉብኝት፣ ሩሲያን የዩክሬን ወራሪ አድርገው የሚያዩትን አብዛኞቹን የአውሮፖ መሪዎች አስቅጥቶ ነበር።
ኦርባን ጉባኝታቸውን በሩሲያ አላበቁም። ከሞስኮ ወደ ቻይና ከዚያም ወደ አሜሪካ በማቅናት ከፕሬዝደንት ባይደን እና ከቀድሞው ፕሬዝደንት ትራምፕ ጋር በሩሲያ- ዩክሬን ጉዳይ መክረዋል።
በዚህ ደብዳቤ ኦርባን ፕሬዝደንት ባይደን በምርጫ ጉዳይ "ያልተቆጠበ ጥረት እያደረጉ" ነው፤ "አሁን ያለውን ጦርነት ደጋፊ የአሜሪካ ፖሊሲ ማስተካከል አይችሉም" ብለዋል።
ኦርባን የአውሮፓ ሀገራት ለዩክሬን የሚያደርጉትን ወታደራዊ ድጋፍ ሌሎች አጋሮቿ ከሚያደርጉት ጋር በማነጻጸር ጠንካራ ትችት በማቅረብ ይታወቃሉ።
"የእኛ የአውሮፓውያን ስትራቴጂ በትራንስአትላንቲክ አንድነት ስም የአሜሪካን ጦርነት ደጋፊ ፖሊሲ እየኮረጅን ነው። የሉአላዊ የሆነ የአውሮፓ ስትራተጂ ወይም የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ እስካሁን የለንም" ብለዋል ኦርባን።
ኦርባን ከዩክሬን ጋር ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ከማስቀጠል ጎን ለጎን ከሩሲያ ጋር ቀጥተኛ የግንኙነት መስመር መክፈት እንደሚያደርግ አመላክተዋል።
ዩክሬን፣ የራሷን የሰላም ጉባኤ በተለያዩ ቦታዎች በማካሄድ በሩሲያ ላይ ጫና ለማሳደር ብትሞክርም፣ በሩሲያ በኩል እስካሁን የአቋም ለውጥ አልታየም።
ሞስኮ፣ ዩክሬን በአሁኑ ወቅት ሩሲያ በከፊል የያዘቻቸውን አራት ግዛቶች ለቃ የምትወጣ ከሆነ ጦርነቱን እናቆመዋለን የሚል አቋም አንጸባርቃለች። ይህን የሩሲያ ቅድመ ሁኔታ "እጅ እንደመስጠት እቆጥረዋለሁ" ያለችው ዩክሬን ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።