ኔቶ የዩክሬን አባልነት ሂደት “የማይቀለበስ” ደረጃ ደርሷል አለ
ኬቭ ከሞስኮ ጋር የገባችበት ጦርነት ካልተጠናቀቀ ግን የሰሜን አትላቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት አባል እንደማትሆን ተገልጿል
32 አባላት ያሉት ወታደራዊ ጥምረት አመታዊ ጉባኤውን ሲጀምር ለዩክሬን የ43 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል
የዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባልነት ሂደት “የማይቀለበስ” ደረጃ መድረሱ ተገለጸ።
32 አባላት ያሉት ወታደራዊ ጥምረት በዋሽንግተን ዲሲ አመታዊ ጉባኤውን ሲያካሂድ ኬቭ ስብስቡን የምትቀላቀልበት ጊዜ ላይ ስምምነት አልተደረሰም።
ኔቶ በጉባኤው ዩክሬን ወታደራዊ ጥምረቱን ለመቀላቀል እያደረገች ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ የዴሞክራሲያዊ እና የደህንነት የሪፎርም ስራዎች ማድነቁን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ የንስ ስቶልተንበርግ ግን ኬቭ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኔቶን እንደማትቀላቀል አስምረውበታል።
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር የገባችበት ጦርነት ከተጠናቀቀና ሞስኮ ዳግም ጥቃት እንደማታደርስባት ካረጋገጠች በኋላ አባል ብትሆን ይመከራል ሲሉም የጸና አቋማቸውን ገልጸዋል።
የኔቶ አባል ሀገራት በጋራ እና በተናጠል ባወጧቸው መግለጫዎች ዩክሬን 33ኛ የኔቶ አባል እንድትሆንና የሩሲያን ጥቃት እንድትመክት የማያቋርጥ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
ስብስቡ የአሜሪካውን ኤፍ- 16 ጄት እና የአየር መቃወሚያዎችን ጨምሮ በቀጣዩ አመት ለኬቭ የ43 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው ያስታወቀው።
ዴንማርክ እና ኔዘርላንድስ ኤፍ-16 ጄቶችን በቅርቡ ወደ ኬቭ እንደሚልኩም ተገልጿል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ኔቶ የኬቭን የአየር ሃይል ለማጠናከር ላሳለፈው ውሳኔ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፥ አሁንም ምዕራባውያን የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙ ተማጽነዋል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ዋነኛ መወያያው አጀንዳው ያደረገው ኔቶ ከሩሲያ ጋር ግጭት ውስጥ መግባት እንደማይፈልግ ነው ባወጣው መግለጫ የጠቆመው።
የኔቶን ወደ ምስራቅ መስፋፋት አጥብቃ የምትቃወመው ሞስኮ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ያስገባት ዋነኛው ጉዳይ ይሄው መሆኑን ስታነሳ ቆይታለች።
ዩክሬን የኔቶ አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት ካቆመች የሰላም ንግግር ለመጀመር ዝግጁ መሆኗንም ለቻይና እና ሃንጋሪ መሪዎች መግለጿ ይታወሳል።