የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚንስትር ቪክተር ኦርባን የዲፕሎማሲ ጉዞ አውሮፓን ለምን አስቆጣ?
በዩክሬን እና ሩስያ መካከል ሰላም ለማውረድ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረጉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚንስትሩ ከአውሮፓ ህብረት ቅሬታ ቀርቦባቸዋል
ዋሽንግተን እና የአውሮፓ አጋሮቿ ዩክሬንን ለማስታጠቅ የተጉትን ያህል የሰላም ድርድሮችን በአማራጭነት ማቅረብ ለምን ተሳናቸው?
የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚንስትር ቪክተር ኦርባን በሩስያ እና ዩክሬን መካከል ሰላምን ለማስፈን ያደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ጉዞ በአውሮፓ ህብረት ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።
የወቅቱ የአውሮፓ ካውንስል ፕሬዝዳንት የሆኑት ጠቅላይ ሚንስትሩ ሁለቱ አካላትን ለማቀራረብ አላማ ባለው ጉዞ ሳይጠበቁ በአራት ወሳኝ ቦታዎች ላይ ተገኝተዋል።
በዩክሬን ፣ ሩስያ ፣ ቻይና እና አሜሪካ ጉብኝት ያደረጉት ኦርባን ጦርነቱን ለማስቆም ከጎበኟቸው ሀገራት መሪዎች ጋር በጥልቀት መክረዋል።
የምስራቅ አውሮፓው ሰው በዩክሬን በተገኙ ጊዜ አድናቆታቸውን የቸሩት የአውሮፓ ህብረት ሀላፊዎች እና ሀገራት በቻይና እና ሩስያ ቀጥሎም በአሜሪካ ያደረጉትን ጉብኝት አልወደዱትም።
ኦርባን በአውሮፓ ህብረት ስም የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወን አይችልም ያሉት ተቃዋሚዎቻቸው ድርጊታቸው ከካውንስሉ ፕሬዘዝዳንትነት ሊያስነሳቸው እንደሚችል ዝተዋል።
የአውሮፓ ሀገራት በጦርነቱ ከየትኛውም አካባቢ የበለጠ የሚጎዱት እነርሱ ሆነው ሳለ ሞስኮ እና ኬቭን ለመቀራረብ ሁነኛ ሙከራ አላደረጉም በሚል የሚከሱት ኦርባን ለዩክሬን ከፍተኛ ወታደራዊ ድጋፍ በማድረግ እና ጦርነቱን በማባባስ ላይ ተጠምደዋል ሲሉ ይከሷቸዋል።
የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጥብቅ ወዳጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዢንፒንግ እና ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ባደረጉት ውይይት የተኩስ አቁም ስምምነት እና ድርድር እስከተያዘው የፈረንጆቹ አመት መጨረሻ ድረስ እንዲካሄድ ፍላጎት እንዳላቸው መረዳታቸውን ገልጸዋል።
ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮላዳይመር ዘለንስኪ ጋር ባደረጉት ቆይታ ፕሬዝዳንቱ ለሰላም ዝግጁ ቢሆንም ፑቲን ባቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች ቅሬታ እንዳላቸው ፣ ድርድር ለመጀመርም የሩስያ ወታደሮች ከዩክሬን ግዛት በቅድሚያ ሊወጡ እንደሚገባ መናገራቸውን ለአውሮፓ ሀብረት አመራሮች ባቀረቡት ሪፖርት አሳውቀዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ኦርባን ከስፔን ጋዜጣ ጋር ያደረጉትን ቆይታ ጠቅሶ ዘገባ የሰራው አርቲ እንዳስነበበው ኦርባን በአንድ ሳምንት ውስጥ ያደረጉትን የዲፕሎማሲ ሙከራ ምዕራባውያን በሁለት አመት ውስጥ አላደረጉም።
በተመድ እና በቱርክ አደራዳሪነት በጥቁር ባህር የእህል ምርቶች ለአለም ገበያ እንዲቀርቡ ካደረጉት ንግግር ባለፈ ዩክሬን እና ሩስያ በሰላም ጉዳይ ፊት ለፊት ተገናኝተው ሁነኛ ውይይት አድርገው አያውቁም።
በኢስታንቡል ዩኒቨርስቲ የሁለተኛው አለም ጦርነት እና የምስራቅ አውሮፓ ታሪክን የሚያስተምሩት ፕሮፌሰር ታሪክ ሲሪል አማር እንደሚሉ የአውሮፓ ህብረትም ሆነ አሜሪካ በዩክሬን ጉዳይ ያፈሰሱት ገንዘብ፣ የተሰበሰቧቸው ጉባኤዎች እና ያጠፉት ጊዜ አንዱም የሰላም አማራጭን አቅጣጫ ያመላከተ አልነበርም።
ዋሽንግተን እና የአውሮፓ አጋሮቿ ዩክሬንን ለማስታጠቅ የተጉትን ያህል የተኩስ አቁም እና የሰላም ድርድሮችን ወደ ጠረጴዛ ማምጣት ቢችሉ ኖሮ ጦርነቱ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ባልደረሰ ነበር ብለዋል ፕሮፌሰሩ።
አክለውም ይህ ጦርነት የአለምን የንግድ ስርአት ከማዛባቱ ባለፈ በአለም አቀፍ ደረጃ የፈጠረው የጦርነት ስጋት ቀላል አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ዩክሬን በማታሸንፈው የተራዘመ ጦርነት ውስጥ እንድትጠፋ ከመፍቀድ ይልቅ ሁሉቱ ተዋጊዎች የሚቀራረቡበትን መንገድ ማበጀት ያሻል ነው ያሉት።
አውሮፓ ከቻይና እና አሜሪካ በበለጠ የዩክሬን እና ሩስያ ጦርነት ይመለከተዋል የሚሉት ኦርባን ሁለቱን ሀገራት በማቀራረቡ ረገድ ቀዳሚውን ሀላፊነት ሊወጣ ይገባል ባይ ናቸው።
ሆኖም ይህ የሰላም ጉዟቸው ምንነቱ በግልጽ ባልታወቀ ሁኔታ በአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮንደርሌይን ፣ በአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሀላፊ ጆሴፍ ቦሬል እና በሌሎች የህብረቱ ከፍተኛ አመራሮች ነቀፌታን አሰንዝሮባቸዋል።