የፑቲን ወዳጅ ቪክቶር ኦርባን ከዜለንስኪ ጋር ለመምከር ኬቭ ገቡ
የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር የአውሮፓ ህብረትና ኔቶ ለዩክሬን የሚያደርጉትን ወታደራዊ ድጋፍ በመቃወም ይታወቃሉ
ኦርባን በኬቭ ጉብኝት በማድረግ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች የመጨረሻው ናቸው
የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚንስትር ቪክቶር ኦርባን ኬቭ ገብተዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ካወጀች ወዲህ በዩክሬን የመጀመሪያውን ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ጋር ይመክራሉ ተብሏል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወዳጅ የሆኑት ኦርባን የአውሮፓ ህብረት እና ኔቶ ለዩክሬን የሚያደርጉትን ድጋፍ በተደጋጋሚ ተቃውመዋል።
በየካቲት ወር 2022 በዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህም ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ከመከሩ ጥቂት የምዕራባውያን መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው።
በብራሰልስ ከተካሄደው የአውሮፓ ህብረት ጉባኤ ከዜለንስኪ ጋር የመከሩት ኦርባን ከየካቲት 2022 ወዲህ በዩክሬን ጉብኝት ያደረጉ የመጨረሻው የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገር መሪ ሆነዋል።
26ቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ለዩክሬን አጋርነታቸውን ለማሳየት በኬቭ ጉብኝት ማድረጋቸውን ፋይናንሽያል ታይምስ አስታውሷል።
የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ግን የአውሮፓ ህብረት ለኬቭ የጦር መሳሪያ ግዥ ድጋፍ የሚውል 6 ነጥብ 6 ቢሊየን ዩሮ እንዳያጸድቅ ሰባት ጊዜ ተቃውመዋል።
ዩክሬን የአውሮፓ ህብረት አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረትም በሀገሪቱ የሚኖሩ የሀንጋሪ ተወላጆችን መብት አላከበረችም በሚል ሲቃወሙ ቆይተው ባለፈው ወር ገደባቸውን ማንሳታቸው ይታወሳል።
ኦርባን ባለፈው ወር በስዊዘርላንድ በተካሄደው የዩክሬን ጉባኤ እንዲሳተፉ በዜለንስኪ የቀረበላቸውን ግብዣ ውድቅ አድርገው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን መላካቸውም አይዘነጋም።
ኬቭም የሩሲያው ፕሬዝዳንት ወዳጅ ሀገር የሆነችው ሀንጋሪ የአውሮፓ ህብረት ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት እንዳትሆን የመከላከል ሙከራ ማድረጓ የሚታወስ ነው።
ኦርባን ለሌሎች የአውሮፓ መሪዎች በኬቭ ላይ የያዙትን አቋም ለማለዘብ በገቡት ቃል መሰረትም ዛሬ ከሩሲያ ጋር እየተዋጋች ወደምትገኘው ዩክሬን አምርተዋል።