ልዩ የጥምቀት በዓል አከባበር በመላው አለም
በሞንቴኔግሮ ወንዝ ውስጥ የተወረወረ መስቀልን ለመያዝ የዋና ውድድር ይካሄዳል
ሩሲያን ጨምሮ በበርካታ የአውሮፓ ሀገራት ደግሞ በዓሉ በበረዶ ውሃ ውስጥ በመነከር ይከበራል
የጥምቀት በዓል ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ተከብሮ ውሏል።
በዓሉ በኤርትራ፣ ሩሲያ፣ ዩክሬን፣ ዮርዳኖስና ሌሎች ሀገራት በተለያዩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶች ተከብሯል።
በዌስትባንክ ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀበት ዮርዳኖስ ወንዝ የጥምቀት በዓል በየአመቱ በድምቀት ያከበራል። ዘንድሮም የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት በተወሰነ መልኩ ቢያደበዝዘውም በዓሉ ተከብሯል።
በሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ጨምሮ ከ90 ሚሊየን በላይ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች የጥምቀት በዓልን የኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቅን ለማስታወስ በበረዶ ውሃ ውስጥ ራሳቸውን ሶስት ጊዜ ይነከራሉ።
በክሬሚያ ለጥቁር ባህር ቅርብ በሆኑ አካባቢዎች የጥምቀት በዓል ሲከበር ህይወት እንዳይጠፋ ጠላቂ ዋናተኞች በብዛት ይሰማራሉ።
በሩሲያዋ መዲና ሞስኮም የእምነቱ ተከታዮች ጥልቀት ባለውና ቀዝቃዛ በሆነ ውሃ ውስጥ ራሳቸውን በመንከር ድህነት እንደሚያገኙ ያምናሉ።
በሞንቴኔግሮ ፖድጎሪካ ከተማ ደግሞ ወደ ሪብኒካ ወንዝ የሚወረወር የእንጨት መስቀልን ለማግኘት የሚደረግ አመታዊ ፉክክር የበዓሉ ድምቀት ሆኖ ቀጥሏል። መስቀሉን የሚያገኘው ሰው አመቱን ሙሉ የተባረከ ይሆናል ተብሎ ይታመናል።
የማዕከላዊ እስያዊቷ ሀገር ካዛኪስታንም በበረዷማ ውሃ ውስጥ በመጠመቅ የኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀት ከሚያከብሩ ሀገራት ተጠቃሽ ናት።