እግር ኳሳችን ትንሳኤ ያስፈልገዋል" - አቶ መላኩ ፈንታ፤ ለኢእፌ ፕሬዝዳንትነት እጩ ተወዳዳሪ
በጎንደር ሊካሄድ የነበረው የፌዴሬሽኑ ጉባዔ በድንገት መቀየሩ "የተለመደውን የምርጫ አካሄድ ለመድገም ነወይ ያስብላል" ብለዋል
ከውድድሩ ራሳቸውን ሊያገሉ ይችላሉ ስለመባሉ አስተባብለዋል
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ትንሳኤ ያስፈልገዋል ሲሉ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት አቶ መላኩ ፋንታ ተናገሩ።
አቶ መላኩ "ትንሳኤ"ውን ለማምጣት የሚያስችል ነው ያሉትንና ፕሬዝዳንት ሆነው ቢመረጡ ሊፈጽሙ የሚችሏቸውን ዝርዝር ተግባራት የያዘ አዲስ ፍኖተ ካርታ ይዘው መምጣታቸውን ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ አድርገዋል።
በፍኖተ ካርታው ስፖርቱን ካለው የገበያ ባህሪ አንጻር በቢዝነስ እሳቤ ጭምር ለመምራት፣ መሠረታዊ ለውጥ በሚያመጣ መንገድ ፌዴሬሽኑን ለማደራጀትና የመፈጸም አቅሙን ለማሳደግ፣ የተንከባለሉ ጉዳዮችን በአጭር ጊዜ በመጨረስ በጎዎቹን ለማስቀጠልና ተቋማዊ ስርዓቱን መልክ ለማስያዝ እሰራለሁ ብለዋል።
የተመረጡ ስታዲየሞች በአጭር ጊዜ ተጠናቀው "ስደተኛው ብሔራዊ ቡድናችን" በሜዳው እንዲጫወት እናደርጋለንም ነው አቶ መላኩ ያሉት።
ተዓማኒ የውድድር ስርዓት እንዲኖር፣ የሴካፋ እና የካፍ ውድድሮችን ለማምጣት ጠንክረን የምንሰራ ይሆናልም ብለዋል።
ስፖርቱ ያለውን ህዝባዊ መሠረት በመጠቀም ታዳጊዎች ላይ ለመስራትና ሙያተኞችን ጭምር ለማሳተፍ የሚያስችሉ ለውጦችን እናደርጋለን ያሉም ሲሆን ከዩኒቨርስቲዎች ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
"ግራስሩት ላይ መስራት፣ መሠረተልማት ማስፋፋት፣ በቢዝነስ ሞዴል መምራት እና የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ" ሲሉም ነው አቶ መላኩ የሚሰሯቸውን ያስቀመጡት።
ሆኖም ይህን ለመለወጥ በቅድሚያ ራሳችን መለወጥ አለብን ያሉት አቶ መላኩ። የእጩዎች ምርጫው ከወትሮው በተለየ መልኩ በግልጽ እና ፍትሐዊ አካሄዶች ሊመራ እንደሚገባም አሳስበዋል።
እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በመጪው ነሐሴ 21 እና 22፣ 2014 ዓ/ም በጎንደር ከተማ ሊያካሂድ የነበረውን ጠቅላላ ጉባኤ ጉባኤውን ለማካሄድ የማያስችሉ ሁኔታዎች መኖራቸውን በመጥቀስ መሠረዙ ይታወሳል። ምንም እንኳን እርምጃውን የአማራ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቢቃወመውም።
የእርምጃውን ስህተትነት እና ኢ ፍትሐዊነት የገለፁት አቶ መላኩም "የተለመደውን የምርጫ አካሄድ ለመድገም ነወይ" ሲሉ የከተማውና የክልሉን ገፅታ ጭምር የሚያበላሽ እንደሆነ ተናግረዋል።
እርምጃው በውድድራቸው ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽዕኖ እንዳለና ከውድድሩ ራሳቸውን ሊያገሉ ይችሉ እንደሆን ለቀረበላቸው ጥያቄ ያን የሚያደርጉበት ምንም ዐይነት ምክንያት እንደሌለ ከእርምጃው ኢ-ፍትሐዊነት ውጪ በየትኛውም የሃገሪቱ አካባቢ ቢካሄድ ቅር የሚላቸው ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።
አቶ መላኩ የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) እንዲሁም የአማራ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ ናቸው። ፋሲል ከነማን በቦርድ አባልነትም ያገለግላሉ።
ይህ ምናልባትም ፌዴሬሽኑን ለመምራት ጫና ይፈጥርባቸው እንደሁ የተጠየቁት አቶ መላኩ
ተቋሙን ለመምራት ፍላጎት ብቻም ሳይሆን በቂ የትምህርት ዝግጅት እና ልምድ እንዳላቸው ገልጸዋል ብዙ ሊያሳድር የሚችልባቸው ተጽዕኖ እንደሌለ በመጠቆም።
ከአሁን ቀደም በሙስና መከሰሳቸው ከውድድሩ ሊያስቀራቸው የሚችልበት ህጋዊ መሠረት እንደሌውም ገልጸዋል።
"በእግር ኳሱ ተቋማትን ለመገንባት የሚያስችሉ መሠረቶችን ጥሎ ማለፍ" እፈልጋለሁም ብለዋል።