በ1 ሳምንት ብቻ ከሊቢያ የባህር ዳርቻ የተነሱ ከ1 ሺህ በላይ ስደተኞችን መታደግ እንደተቻለ ተገለፀ
የፈረንጆቹ 2021 ከገባ ጀምሮ እስከሁን ባለው ጊዜ 19 ሺህ 393 ህገ ወጥ ስደተኞችን መታደግ ተችሏል
ባለፉት 7 ወራት ብቻ የ360 ስደተኞች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ 570 ስደተኞች ደግሞ ጠፍተዋል
በሳለፍነው አንድ ሳምንት ውስጥ ከ1 ሺህ በላይ ስደተኞችን ከሊቢያ የባህር ዳርቻ ላይ መታደግ እንደተቻለ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት አስታወቀ።
በህገ ወጥ መንግድ በሜድትራኒያን ባህር አድርገው ወደ አውሮፓ ሊሸገሩ የነበሩት ስደተኞቹ ወደ ሊቢያ እንዲመለሱ መደረጉንም ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
እንደ ድርጅቱ ተገለጻ፤ ከሐምሌ 18 እስከ ሐምሌ 14 ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ 1 ሺህ 111 ህገ ወጥ ስደተኞችን መታደግ የተቻለ ሲሆን፤ ሁሉም ስደተኞች ወደ ሊቢያ ተመልሰዋል።
የፈረንጆቹ 2021 ከገባ ጊዜ ጀምሮ እስከሁን ባለው ጊዜ ብቻ ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ 19 ሺህ 393 ህገ ወጥ ስደተኞችን መታደግ እንደተቻለም ነው የተገለጸው።
በሊቢያ የባር ዳርቻ ላይ ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ የ360 ስደተኞች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ 570 ስደተኞች ደግሞ እስካሁን የገቡበት እንዳልታወቀ ነው ሪፖርቱ ያመላከተው።
በፈረንጆቹ 2011 የሊቢያው መሪ ሙአማር ጋዳፊ ከስልጣን ከተነሱ በኋላ ሀገሪቱ ወደ አለመረጋጋት እና ትርምስ ውስጥ መግባቷ ይታወቃል።
ይህንን ተከትሎም ሊቢያ በአሁኑ ጊዜ ህገ ወጥ ስደተኞች ሜድትራኒያን ባህርን በማቋረጥ ወደ አውሮፓ ለመድረስ ለሚያደርጉት ጉዞ ተመራጭ ስፍራ ሆናለች።
በሊቢያ የሚገኙ የስደተኛ መጠለያዎች ባህር ከመስጠም በዳኑ ወይንም በሊቢያ የጸጥታ ኋይሎች በተያዙ ስደተኞች የተሞሉ ናቸው፡፡