ከወር በፊት በደረሰ ተመሳሳይ አደጋም የ20 ስደተኞች ህይወት አልፏል
በጅቡቲ ስደተኞችን የጫነች ጀልባ ሰጥማ የ34 ስደተኞች ህይወት ማለፉን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት አስታወቀ።
በጅቡቲ የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ባለስልጣን ከአደጋው የተረፉ ስደተኞችን በመጥቀስ እንዳስታወቀው፤ ጀልባዋ 60 ስደተኞችን ጭና ወደ የመን በመጓዝ ላይ እያለች መስጠሟን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
ስደተኞቹ በህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ምክንያት በመጓጓዝ ላይ እንደነበሩ የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ሞሀመድ አብዲከድር አስታውቀዋል።
በአደጋው ህይወታቸውን ካጡት ውስጥ አብዛኞቹ ህፃናት መሆናቸውን ያስታወቁት የድርጅቱ የስራ ኃላፊዎች፤ ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ህክምና እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከወር በፊትም በደረሰ ተመሳሳይ አደጋ የ20 ስደተኞች ህይወት ማለፉን እና በርካቶች መቁሰላቸውንም ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።
ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል እና በህግ ተጠያቂ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባውም የፍልሰተኞች ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ሞሀመድ አብዲከድር ተናግረዋል።
በጀልባዋ መስጠም ህይወታቸው ስላለፈ ስደተኞች ዜግነት በዘገባው የተባለ ነገር የለም፡፡