በአንድ ቀን ብቻ 1ሺህ 200 ስደተኞች ጣሊያን ገቡ
ጣሊያን ሰሞኑን ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ስደተኞች መጨናነቋ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ ተስተውለዋል
በ2021 ብቻ ባህር እና ውቅያኖስ ውስጥ ከ3ሺህ 200 በላይ ሰዎች መሞታቸው የተመድ መረጃ ያመለክታል
በ24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ 1 ሺ 200 ስደተኞች በሲሲሊ ወደቦች በኩል በጀልባዎች ተጭነው ጣሊያን መግባታቸው የጣሊያን መንግስት አስታወቀ፡፡
ስደተኞቹ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ሲሆን እስያ፣ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የተውጣጡ ናቸው ተብለዋል፡፡
ስደተኞቹ በዋናነት ከአፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን፣ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የመጡ መሆናቸውን የሀገሪቱ በነፍስ አድን ሰራተኞች ገልጸዋል ሲል ፍራንስ 24 ዘግቧል።
የጣሊያን የነፍስ አድን ባለስልጣናት በበኩላቸው ፤በካላብሪያ የባህር ዳርቻ ብቻ 674 ሰዎችን የተቀበሉ ሲሆን፤ አምስት አስከሬኖችም ከስደተኞቹ ጋር በሰው በተጨናነቁት የአሳ ማጥመጃ ጀልባዎች ላይ ተጭነው መገኘታቸው አስታውቋል፡፡
በ15 ጀልባዎች ተጭነው የመጡ 522 ስደተኞች ባሳለፈነው ቅዳሜ ወደ ላምፔዱሳ ወደብ መድረሳቸውም ባለስልጣናቱ ተናግረዋል፡፡
ላምፔዱሳ ከሊቢያ እና ቱኒዝያ በመነሳት አውሮፓ ድረስ የሚዘልቁ ጀልባዎች የሚሳፈሩ ስደተኞች እንደዋነኛ መዳረሻ ከሚያደርጓቸው ወደቦች አንዱ ነው፡፡
ጣሊያን ሶሞኑን ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ስደተኞች መጨናነቋ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ ተስተውለዋል፡፡
በሲሲሊ በሚገኘውና 350 ሰዎች ብቻ የመያዝ አቅም እንዳለው በሚነገርለት የስደተኞች ማዕከል ብቻ 1 ሺህ 184 ሰዎች እንደሚገኙም አንሳ የተባለ አንድ የጣሊያን ሚዲያ ዘግቧል፡፡
ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ ህገ-ወጥ በሆነ መልኩ በባህር ላይ ለመግባት የሚደረግ ጉዞ እጅጉን አደገኛ መሆኑ ይገለጻል፡፡
በመቶ ሺዎች ሚቆጠሩ ስደተኞች ህይወታቸው ያጡበት መንገድም ነው፡፡
በ2021 በሜዲትራኒያን ባህር እና በሰሜን ምዕራብ አትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ ከ3ሺህ 200 በላይ ሰዎች መሞታቸው ወይም ጠፍተዋል ተብለው መመዝገባቸው የተመድ መረጃ ያመለክታል፡፡
በርካቶችም በባህር ጉዞ ላይ ሳሉ ጀልባዎች ተበላሽተው በመሃል ህይወታቸው ያለፈ መሆኑ ይነገራል፡፡