ከሰሞኑ ኢትዮጵያ የነበሩት የጣሊያን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ከመሪው የሃገሪቱ ጥምር ፓርቲ ሊለቁ ነው
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ ጉዳይ ነው ከፓርቲያቸው የሚለቁት
ዲ ማዮ ከ'ፋይቭ ስታር' ፓርቲ ለመልቀቅ መወሠናቸውን አስታውቀዋል
ከሰሞኑ ኢትዮጵያ የነበሩት የጣሊያን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊውጂ ዲ ማዮ ከ'ፋይቭ ስታር' ፓርቲ ሊለቁ መሆኑን ገለጹ።
'ፋይቭ ስታር' በጠቅላይ ሚኒስትር ማቲዮ ድራጊ ጥምር የጣሊያን መንግስት ውስጥ ትልቁ አጣማሪ ፓርቲ ነው።
ሆኖም ከዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲ ማዮ ፓርቲውን ለቀው እንዲወጡ አስገድዷል።
መከፋፈሉ ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ መደረግ አለበት የለበትም በሚል የተፈጠረ ነው።
ወታደራዊ ድጋፉ መደረግ አለበት፤ በዚህ ወሳኝ ጊዜ ከመንግስትና ከአውሮፓ ጎን ቆመን እርምጃዎቹን ልንደግፍ እንጂ ልንሸሽ አይገባም ያሉት ዲ ማዮ ይመሩት የነበረውን ፓርቲ ለቀው መውጣትን መርጠዋል።
የፓርቲው የወቅቱ መሪ የቀድሞው የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ በበኩላቸው ጣሊያን ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍን ልታደርግ አይገባም ባይ ናቸው።
ሆኖም ይህ አቋማቸው በቅርቡ ኪቭን ከጎበኙት እና ወታደራዊ ድጋፍን ለማድረግ ቃል ከገቡት ከጠቅላይ ሚኒስትር ድራጊ ይቃረናል።
ድራጊ ዩክሬን የአውሮፓ ህብረት አባል ለመሆን ያቀረበችውን ሃሳባ መደገፋቸውም አይዘነጋም።
ይህ ግን በትልቁ አጣማሪ ፓርቲያቸው ውስጥ ብቻም ሳይሆን በጣሊያናውያን መካከልም ሁነኛ መከፋፈልን ፈጥሯል።
እርምጃውን የደገፉት ዲ ማዮም የራሳቸውን አዲስ ቡድን ለማቋቋም መወሰናቸውን አስታውቀዋል። ወደ ሐገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት ከገቡ 227 የ'ፋይቭ ስታር' አባላት መካከል 60ዎቹ ዲ ማዮን መደገፋቸውም ነው የተነገረው።
ፓርቲው ከድራጊ ጥምር መንግስት የመለያየት ውጥን የለውም። ሆኖም ሊቀመንበሩ ኮንቴ ከኃላፊነታቸው ሊለቁና ከድራጊ ጥምር መንግስት ራሳቸውን አግልለው በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ ጊዜያዊ ድጋፍ ለማድረግ መወሰናቸው ተሰምቷል።
ህዝበኛ (ፖፑሊስት) ስለመሆኑ የሚነገርለት 'ፋይቭ ስታር' ፓርቲ በነበረው ተቀባይ በፈረንጆቹ 2018 ወደ ስልጣን መምጣቱ ይታወሳል።
ጁሴፔ ኮንቴም በኮሮና ወረርሽኝ ክፉኛ ተፈትነው ስልጣን እስከለቀቁበት ጊዜ ድረስ ጣሊያንን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መምራታቸው ይታወሳል።
ከሰሞኑ በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ሌሎችም ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ያወሩት ዲ ማዮ የ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገደማ የረጅም ጊዜ ብድር ስምምነት መፈራረማቸው አይዘነጋም።