በአሜሪካ አውሮፕላን ጣቢያዎች ላይ ባጋጠመ አደጋ ከ12 ሺህ በላይ በረራዎች ተስተጓጎሉ
በረራዎች እየተሰረዙ ያሉት በአውሮፕላን ጣቢያዎች ላይ ባጋጠመ የቴክኒክ ብልሽት ነው ተብሏል
የአሜሪካ አቪዬሽን ባለስልጣን በበኩሉ የሳይበር ጥቃት አልተፈጸመብኝም ሲል አስተባብሏል
የዓለማችን ልዕለ ሀይል በሆነችው አሜሪካ የአየር ትራፊክ አልታዘዝም ማለቱን ተከትሎ አውሮፕላን ጣቢያዎች ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸውን በርካታ የዓለማችን ብዙሃን መገናኛዎች በሰበር ዜና እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡
የሀገሪቱ አቪዬሽን ባለስልጣን እንዳለው እስካሁን የደረሰብኝ የበይነ መረብ ጥቃት የለም ቢልም በርካቶች ግን የሳይበር ጥቃት ካልተፈጸመ የአየር ትራፊክ አልታዘዝም ሊል አይችልም እያሉ ነው፡፡
በዋሸንግተን ያለው የአልአረቢያ ጋዜጠኛ እንደዘገበው ከሆነ እስካሁን ከ12 ሺህ በላይ በረራዎች የመሰረዝ እና መስተጓጎል አጋጥሟቸዋል፡፡
የአሜሪካው ኤንቢሲ በበኩሉ ከ1 ሺህ በላይ በረራዎች መሰረዛቸውን፣ የሀገር ውስጥ በረራዎች ሙሉ ለሙሉ እንዲቆም መወሰኑን በሰበር ዜናው ዘግቧል፡
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው የሀገሪቱ ትራንስፖርት ባለስልጣን አስቸኳይ ምርመራ እንዲያደርግ ስለማዘዛቸው ተገልጿል፡፡
እንዲሁም በአሜሪካ የአየር ክልል ውስጥ ያሉ ሁሉም አውሮፕላኖች በረራቸውን አቋርጠው ወደ ምድር እንዲያርፉ በማድረግ ላይ ናቸውም ተብሏል፡፡
መረጃዎች በየጊዜው እየተቀያየሩ ሲሆን ከ3 ሺህ 700 በላይ በረራዎች መዘግየታቸውን እና 567 በረራዎች ደግሞ መሰረዛቸውን የአሜሪካ ነጩ ቤተመንግስት ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
በአሜሪካ የገጠመው የአሁኑ የአቪዬሽን ችግር የዓለምን የአውሮፕላን በረራ ያስተጓጎለ ሲሆን በተለይም ፈረንሳይ እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት በአሜሪካ ያጋጠመው ችግር በግልጽ እስከሚታወቅ ድረስ በረራዎች እንዲዘገዩ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
የአሜሪካ አቪሽን ባለስልጣን በበኩሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያጋጠመው የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያው የቴክኒክ ብልሽት እንዳጋጠመ ገልጾ ሁሉም በረራዎች እንዲዘገዩ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡