የሩሲያው አዙር አየር መንገድ አውሮፕላን በቦምብ አደጋ ስጋት ምክንያት በረራውን አቋረጠ
አውሮፕላኑ ከሞስኮ ወደ ህንድ መዲና በመብረር ላይ ነበር ተብሏል
አውሮፕላኑ በደረሰው ድንገተኛ የቦምብ ጥቃት መልእክት ምክንያት በህንድ ወታደራዊ ኤርፖርት ለማረፍ ተገዷል
የሩሲያው አዙር አየር መንገድ አውሮፕላን በቦምብ አደጋ ስጋት ምክንያት በረራውን አቋረጠ፡፡
የሩሲያ ንብረት የሆነው አዙር አየር መንገድ አውሮፕላን በዛሬው ዕለት ከሞስኮ ወደ ሕንድ በመደበኛ በረራው ላይ ነበር፡፡ ይህ አውሮፕላኑ ከሩሲያ መዲና ሞስኮ ወደ ሕንዷ ጓዓ ከተማ በመብረር ላይ እያለ የአደጋ መልዕክት ይደርሰዋል።
መልዕክቱም በተሳፋሪዎች ሻንጣ ውስጥ የተደበቀ ቦምብ እንዳለ የሚገልጽ ሲሆን ለደህንነት በሚል ጃማንጋር ወደተሰኘው የህንድ ወታደራዊ ማዘዣ ለማረፍ ተገዷል፡፡
የሕንድ ጸረ ሽብር ቡድን ባደረገው ማጣራትም በአውሮፕላኑ ውስጥ የተቀመጠ ቦምብ አለመኖሩን አረጋግጧል ሲል ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
የሀገሪቱ የጸረ ሽብር ቡድን አውሮፕላኑን በጉጃራት አየር ሀይል ማዘዣ ውስጥ እንዲያርፍ ካደረገ በኋላ የተሳፋሪዎችን ሻንጣ እና በሌሎችም የአውሮፕላኑ ክፍል ውስጥ ፍተሸ አድርጎ የተገኘ ጎጂ ነገር አለሞኖሩን አረጋግጧልም ተብሏል፡፡
በሕንድ የሩሲያ ኢምባሲ በትዊተር ገጹ ላይ ባጋራው መረጃ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ሁሉም ተሳፋሪዎች ምንም አይነት ችግር እንዳልደረሰባቸው ገልጿል፡፡
ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ ያለችው ሩሲያ በምዕራባዊያን ድጋፍ የሰለጠኑ ዩክሬናዊያን በረቀቀ መንገድ በሞስኮ ዋና ዋና መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሙከራዎች አሉ ማለቷ ይታወሳል፡፡
በፈረንጆቹ 2014 በህዝበ ውሳኔ ወደ ሩሲያ የተቀላቀለችው ክሪሚያን ከተቀረው የሩሲያ ከተሞች ጋር የሚያስተሳስረውን ፈጣን መንገድ ላይ ከሁለት ወር በፊት ፍንዳታ መድረሱም አይዘነጋም፡፡
የዩክሬን ይሄንን አደጋ ስለማድሯ እስካሁን ሃላፊነት ባትወስድም የረቀቁ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም በሩሲያ ዋና ዋና መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ላይ መሆኗን ተናግራለች፡፡