ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በዓለም ላይ ከ1 ሺህ 400 በላይ ጋዜጠኞች መገደላቸው ተገለጸ
ባለፉት አራት ወራት ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ 16 ጋዜጠኞች ተገድለዋል ተብሏል
ዓለምአቀፉ የሚዲያ ነጻነት ቀን በዛሬው እለት ተከብሯል
ባለፉት አራት ወራት ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ 16 ጋዜጠኞች መገደላቸው ተገለጸ
ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ጥበቃ ላይ የሚሰራው ሲፒጂ የዓለም የሚዲያ ነጻነት ቀንን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ከፈረንጆቹ 1992 ጀምሮ 1442 ጋዜጠኞች በሙያቸው ምክንያት ተገድለዋል፡፡
እንደ ድርጅቱ ሪፖርት ከሆነ በያዝነው 2022 ዓመት ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ብቻ 16 ጋዜጠኞች የተገደሉ ሲሆን የ11 ጋዜጠኞች ግድያ ደግሞ በመጣራት ላይ ነው፡፡
በኢትዮጵያም በ1998 ዓ.ም የአገሬ ሚዲያ ጋዜጠኛ አባይ ሀይሉ በስራ ላይ እያሉ እንዲሁም የኦሮሚያ ብሮድካስት ኔትወርክ (ኦቢኤን) ጋዜጠኛ ሲሳይ ፊዳ ደግሞ ባሳለፍነው ዓመት መገደላቸውን በድርጅቱ ሪፖርት ላይ ተገልጿል፡፡
በ2006 ዓመት 76 ጋዜጠኞች የተገደሉ ሲሆን ይህ ዓመት በታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞች የተገደሉበት ዓመት ተብሎ ተመዝግቧል፡፡
በፈረንጆቹ 2002 ላይ ደግሞ 21 ጋዜጠኞች ሲገደሉ ይህ ዓመት በታሪክ በአንጻራዊነት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞች የተገደሉበት ዓመት ተብሎ ተመዝግቧል፡፡
ኢራቅ፣ ቱርክ፣ ሶሪያ፣ ሩሲያ ፣ሶማሊያ፣ ሜክሲኮ እና አፍጋኒስታን በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ቁጥር ያለው ጋዜጠኞች የተገደሉባቸው ሀገራት ሲሆኑ ከአፍሪካ ደግሞ ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ፣ሴራሊዮን፣ግብጽ እና ናይጀሪያ ብዙ ቁጥር ያለው ጋዜጠኛ የተገደለባቸው ሀገራት ናቸው፡፡