የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትናንት በዋለው ችሎት ጋዜጠኛው በዋስ እንዲለቀቅ ወስኗል'
ከታህሳስ አንድ ቀን ጀምሮ በእስር ላይ የቆየው የተራራ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና አዘጋጅ ታምራት ነገራ ከእስር መለቀቁን ባለቤቱ ለአል ዐይን አማርኛ አስታወቀች።
ላለፉት ወራት በኦሮሚያ ክልል በእስር ላይ የነበረው የተራራ ኔትዎርክ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ዛሬ በ 50 ሺ ብር ዋስ ነው የተለቀቀው ተብሏል።
በዳለቲ ማረሚያ ቤት ከሶስት ወራት በላይ በእስር ላይ የቆየው ታምራት ነገራ የታሰረ ሰሞን የት እንዳለ ሳይታወቅ መቆየቱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጾ እንደነበር ይታወሳል።
ከመጋቢት 2 ቀን 2014ዓ.ም ጀምሮ የጋዜጠኛውን የዋስ መብት ጥያቄ ሲመረምር የቆየው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በትላንትናው ዕለት በዋለው ችሎት ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ በ50 ሺ ብር ዋስ ከእስር እንዲለቀቅ መወሰኑ ይታወሳል።
በዚህም መሠረት ዛሬ መጋቢት 28 ቀን 2014 ዓ.ም ሳኔው ተፈጻሚ ሆኗል።
ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ከዘጠኝ ዓመታት የስደት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ተራራ ኔትዎርክ የተሰኘ የበይነ-መረብ መገናኛ ብዙሃን በማቋቋም እየሰራ ነበር።