ኢሰመኮ፤ የጋዜጠኛ ታምራት ነገራ እስር “ስልጣንን አላግባብ የመጠቀምና ፍትሕን የማጉደል ነው” አለ
ከአዋጁ አተገባበር ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ስር የዋሉና አሁንም ያልተለቀቁ ሰዎች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ ጠይቆ ነበር
ታምራት ነገራ ከታሰረ ሁለት ወራት አልፈዋል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፤ የጋዜጠኛ ታምራት ነገራ እስር “ስልጣንን አላግባብ የመጠቀም እና ግልፅ የሆነ የፍትሕን መጓደል መሆኑን አስታወቀ።
ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ሁለት ወር ከ 10 ቀን ለሚሆን ገሂዜ በእስር ላይ መቆየቱን የገለጸው ኢሰመኮ ጋዜጠኛውን ጨምሮ ልክ እንደ እርሱ ሁሉ ያለአግባብ የታሰሩ አካላት ያለቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ አሳስቧል።
ለዚህን ያህል ጊዜ በእስር ላይ ማቆየት ይቅርና በጋዜጠኝነት ስራ መጓደል የተጠረጠረ ግለሰብም ቢሆን ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት የሚታሰርበት አሳማኝ ምክንያት እንደሌለም ኢሰመኮ ገልጿል።
ከጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተለይም በሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ እንዲነሳ መወሰኑን ኮሚሽኑ በበጎ እንደሚመለከተውም አስታውቆ ነበር።
ኮሚሽኑ፤ በአስቸኳይ ሁኔታ ወቅት ከአዋጁ አተገባበር ጋር ተያይዞ በቁጥጥር የዋሉ እና አሁንም ያልተለቀቁ ሰዎች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ መንግስትን በድጋሚ ጠይቆ ነበር።
በተጨማሪም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቁጥጥር ስር ውለው የተለቀቁ ሰዎችም በእስር ስለመቆየታቸው ማረጋገጫ ባለማግኘታቸው ወደ ስራ መመለስ አለመቻልን ጨምሮ ለተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መጋለጣቸውን ባደረገው ክትትል መገንዘቡንም ኮሚሽኑ ገልጾ እንደነበር ይታወሳል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባሳለፍነው ጥር 18 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጊዜው ሳይደርስ ቀደም ብሎ እንዲነሳ ውሳኔ አሳልፎ፣ ፓርላማውም ይህንኑ ውሳኔ አጽድቆታል።