ኮሚሽኑ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ በአሁኑ ወቅት የት እንደሚገኝ እንደማይታወቅ ገልጿል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እስር እንዳሳሰበው ገለጸ፡፡
ኢሰመኮ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንን ምክንያት በማድረግ ባለፈው ዓመት ጋዜጠኞች እና የሚዲያ አካላት ያለ ፍትህ ሂደት መታሰራቸው እንዳሳሰበው ለአፍሪካ የሰብአዊ እና የህዝቦች መብት ኮሚሽን ጠንከር ያለ መግለጫ መስጠቱን ያስታወሱት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንዔል በቀለ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በታሰረው በጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ሁኔታ መስጋታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ከትናንት በስቲያ እሁድ ሲቪል በለበሱ ሰዎች መወሰዱን የገለጹም ሲሆን መግለጫውን እስከሰጡበት ጊዜ ድረስ ጋዜጠኛው በምን ሁኔታ ላይ እንዳለና የት እንደሚገኝ እንደማይታወቅም ነው ያስታወቁት፡፡
ኢሰመኮ፤ የጋዜጠኛ ታምራት ነገራ እስር “ስልጣንን አላግባብ የመጠቀምና ፍትሕን የማጉደል ነው” አለ
ኮሚሽነር ዳንዔል በእስር ላይ ያሉ ጋዜጠኞችን እና የሚዲያ አካላትን ሁኔታ መከታሉ የፕሬስ ነፃነት አንዱ አካል መሆኑን በመጠቆምም አጠቃላይ የሚዲያ ምህዳሩ በተለያዩ መንገዶች ተጽዕኖ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ለዚህም የታክስ፣ የወጪ፣ የመረጃ አቅርቦት፣ የዐቅም እና የመሰረተ ልማት ጉዳዮችንም በማሳያነት አንስተዋል፡፡
ይህ መንግስትን ጨምሮ በዘርፉ የተሰማሩ የሲቪል ማህበረሰብ አካላትን የተቀናጀ ስራ የሚጠይቅ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ከአሁን ቀደም የኢሳት ጋዜጠኛ የነበረው ጎበዜ ሲሳይ አሁን ላይ በዲጂታል የሚዲያ ዘርፍ በግል ተሰማርቶ ይሰራ ነበር፡፡
የጋዜጠኛውን እስር በተመለከተ ከመንግስትም ሆነ ከጸጥታ አካላቱ የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም፡፡