በፓኪስታን ቅዱስ ቁርአን አቃጥሏል የተባለ ጎብኝ ተገደለ
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጎብኝው በቁጥጥር ስር ከዋለበት ፖሊስ ጣቢያ አስወጥተው በደቦ እንደገደሉት ተገልጿል
ፖሊስ በደቦ ግድያው የተሳተፉትን ሰዎች በቁጥጥር ስር አላዋለም ተብሏል
በፓኪስታን ቅዱስ ቁርአን አቃጧል የተባለ ጎብኝ በደቦ ተገደለ።
ሞሀመድ ኢስማኤል የተባለ ግለሰብ በፓኪስታን ታዋቂ በሆነው የቱሪስት መዳረሻ ማድያን ያቀናል።
በምስራቃዊ ፑንጃብ ግዛት ነዋሪ የሆነው ሞሀመድ ጉብኝቱን ማድረግ እንደጀመረ ግን በሆቴል ውስጥ የቁርአን ገጾችን አቃጥሏል በሚል ተወንጅሏል።
ፖሊስ ግለሰቡን ከደቦ ግድያ መታደግ ችሎ ወደ ጣቢያ ወስዶ ምርመራ እንደጀመረም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ፖሊስ ጣቢያው በማምራት አሳልፈው እንዲሰጧቸው መጠየቃቸውን ዛሂድ ካን የተባሉ የፖሊስ አዛዥ ተናግረዋል።
የፖሊስ ጣቢያውን በማቃጠል ተጠርጣሪውን በእጃቸው ያስገቡት በቁጣ የተሰባሰቡ ሰዎች ሞሀመድ ኢስማኤልን ገድለው አስከሬኑን ማቃጠላቸውንም ነው አዛዡ የገለጹት።
በደቦ ጥቃቱ በበርካታ ፖሊሶች ላይም ጉዳት ነው የተነገረው።
ፖሊስ ከጥቃት አድራሾቹ ውስጥ አንዱንም እስካሁን በቁጥጥር ስር አላዋለም ብሏል ዋሽንግተን ፖስት በዘገባው።
በፓኪስታን ሃይማኖትን የሚያንቋሽሹ ስድቦችና ድርጊቶች በሞት ያስቀጣሉ።
ቅጣቱ በተለምዶ የሚፈጸመው ግን ባልተረጋገጠ ክሶች የተወነጀሉት ሰዎች ጉዳያቸው በህጋዊ አግባብ ታይቶ ሳይሆን በደቦ ፍርድ ነው።
ባለፈው ወርም በፑንጃብ ግዛት የቅዱስ ቁርአን ገጾችን አቃጠለዋል በሚል የተወነጀሉት የ72 አመት አዛውንት የደቦ ጥቃት ተፈጽሞባቸው ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።