ቡድኑ የባሎቺስታን ግዛት ነጻ ሀገር እንድትሆን የሚንቀሳቀስ ሲሆን በነሃሴ ወር የ73 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል
በፓኪስታን በባቡር ጣቢያ ላይ የተፈጸመ የቦምብ ጥቃት በጥቂቱ የ24 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነገረ።
በደቡብ ምዕራብ ፓኪስታን ከምትገኘው ኩዌታ ወደ ፔሻዋር ጉዞ ሊጀምር በተዘጋጀ ባቡር ላይ ነው የቦምብ ጥቃቱ የተፈጸመው።
በዚህም ከ40 በላይ ሰዎች ቆስለው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የባሎቺስታን ግዛት ፖሊስ ዋና አዛዥ ሙዛም ጃህ አንሳሪ ተናግረዋል።
አብዛኞቹ የቆሰሉት ሰዎች ለህይወታቸው አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ መገኘታቸውን በመጥቀስም የሟቾቹ ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ጠቁመዋል።
የቦምብ ፍንዳታው ከ6 እስከ 8 ኪሎግራም የሚመዝን ፈንጂ በታጠቀ አጥፍቶ ጠፊ መፈጸሙንና ከንጹሃን ባሻገር የጸጥታ አካላትም ከሟቾች እና ከቆሰሉት መካከል እንደሚገኙበት ነው የተገለጸው።
የባሎቺ ነጻነት ጦር ለቦምብ ጥቃቱ ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ለሬውተርስ በላከው የኢሜል መልዕክት አስታውቋል።
ቡድኑ 15 ሚሊየን ህዝብ የሚኖርባትና ከአፍጋኒስታን እና ኢራን ጋር የምትዋሰነው ባሎቺስታን ነጻ ሀገር እንድትሆን ነፍጥ አንስቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ ከአስር አመት በላይ ሆኖታል።
በነዳጅና በሌሎች የማዕድን ሀብቶች የበለጸገችው ባሎቺስታን ያለአግባብ እየተበዘበዘች ነው የሚለው ቡድኑ በፓኪስታን መንግስት ተቋማትና ሰራተኞች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ፈጽሟል።
የቡድኑ ታጣቂዎች በነሃሴ ወር 2024 በባሎቺስታን ግዛት በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎችና የባቡር ጣቢያዎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት በጥቂቱ የ73 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።
አስገንጣይ ቡድኑ ቻይና የጀመረቻቸውን የወርቅ እና መዳብ ማውጫዎች እንዲሁም የወደብ ግንባታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለማቋረጥ ያለሙ ጥቃቶችንም በማድረስ ላይ ነው።
የቡድኑ ጥቃት አልሚዎች በማዕድን ሃብቷ ወደበለጸገችው ባሎቺስታን እንዳያመሩ እንቅፋት ከመሆኑ ባሻገር የበርካታ ንጹሃንን ህይወት እየቀጠፈ ይገኛል።