ከእስር ቤት ጠባቂ ሽጉጥ ነጥቀው ያመለጡት የፓኪስታን እስረኞች
በትላንትናው እለት 18 የፓኪስታን እስረኞች ከእስር ቤት አምልጠዋል
በአለም አቀፍ ደረጃ 11.5 ሚሊየን እስረኞች ሲኖሩ አሜሪካ በርካታ እስረኞችን በመያዝ ከአለም ቀዳሚዋ ናት
ፓኪስታን ከምታስተዳድረው የካሽሚር ግዛት 18 እስረኞች ማምለጣቸው ተነገረ፡፡
እስረኞቹ የማረሚያቤት ጠባቂ ሽጉጥ በመቀማት አስፈራርተው ከእስር ቤት ማመለጣቸው ነው የተሰማው፡፡ ራዋላኮት ከተሰኝው እስር ቤት ካመለጡት እስረኞች መካከል ስድስቱ የሞት ፍርደኞች ሲሆኑ ሶስቱ ደግሞ የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት የተፈረደባቸው እንደሆኑ ታውቋል፡፡
የአካባቢው ፖሊስ አዛዥ ሪያዝ ሙግሀል ከእስረኞቹ መካከል አንድኛው ከፖሊስ በተተኮሰበት ጥይት ህይወቱ ማለፉን የተናገሩ ሲሆን ቀሪዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከፍተኛ አሰሳ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መሰል የእስረኞች ማምለጥ በፓኪስታን ያልተለመደ በመሆኑ ጉዳዩ አጋጣሚ ወይስ ታስቦበት የተደረገ ነው በሚል ምርመራ እየተከናወነ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
እስረኞቹ በወቅቱ በጥበቃ ላይ የነበረ የማረሚያ ቤት ፖሊስ እጅ ላይ ሽጉጥ በመንጠቅ ከእስር ቤት ማምለጣቸው ሲነገር ሁኔታው አጋጣሚ ስለ መሆኑ ከፍተኛ ጥርጣሬን አጭሯል፡፡
በአሁኑ ወቅት የእስር ቤቱን ዋና ሃላፊ ጨምሮ በቀኑ ተረኛ የነበሩ ጠባቂዎች ከስራ የታገዱ ሲሆን ምርመራው በነዚህ አከላት ላይ ያተኩራል ነው የተባለው፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ 11.5 ሚሊየን እስረኞች ሲኖሩ አሜሪካ በቁጥር ቀዳሚዋ ናት በሀገሪቱ 1.8 ሚሊየን የሚጠጉ እስረኞች የሚገኙባት ሲሆን ቻይና በ1.7 ሚሊየን እስረኞች ትከተላለች፡፡
ብራዚል ፣ ህንድ ፣ ቱርክ ፣ ሩሲያ እና ሜክሲኮ በርካታ እስረኞች ከሚገኙባቸው ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በየአመቱ በአለም አቀፍ ደረጃ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ከተለያዩ እስር ቤቶች ያመልጣሉ፡፡
ጠንካራ የእስር ቤት ጥበቃ እና ስርአት እንዳላት የሚነገርላት አሜሪካ በአለም አቀፍ ደረጃ በርካታ እስረኞች ከሚያመልጡባቸው ሀገራት መከካል በአንደኛ ደረጃ ትገኛለች፡፡ በ2019 ከአሜሪካ የተለያዩ እስር ቤቶች 2231 እስረኞች ማምለጥ ችለው ነበር፡፡
ጤናማ የእስረኞች ምጣኔ ከመቶሺህ ሰዎች መካከል 140 ሰዎች ብቻ ሊሆኑ እንደሚገባ የሚነገረው የመንግስታቱ ድርጅት፤
ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖር እንዲሁም ሰዎች ህግን በራሳቸው እጅ ለማስከበር የሚወስዱት እርምጃ መጨመር ወንጀሎች እንዲበራከቱ እና የእስረኞች ቁጥርም በዛው ልክ እንዲያሻቅብ ምክንያት መሆኑን ድርጅቱ በስጋት መልክ ያነሳዋል፡፡