በፓኪስታን መስጂድ ውስጥ በደረሰ የቦምብ ጥቃት በጥቂቱ 28 ሰዎችን ተገደሉ
በፔሽዋር ከተማ በተፈጸመው ጥቃት ከ150 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውም ተነግሯል
ለጥቃቱ እስካሁን ሃላፊነት የወሰደ አካል የለም
በሰሜን ምዕራቧ የፓኪስታን ከተማ ፔሽዋር በአንድ መስጂድ ውስጥ የደረሰ ፍንዳታ በጥቂቱ 28 ሰዎች ህይወታቸው እንዲያልፍ አድርጓል።
ከ150 በላይ ሰዎችም የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ነው የፓኪስታን መንግስት ያስታወቀው።
ከከተማዋ ፖሊስ ጣቢያ ህንጻ አጠገብ በሚገኘው መስጂድ ውስጥ ከ260 በላይ ሰዎች በጸሎት ላይ እያሉ ነው ጥቃቱ የተፈጸመው።
የቦምብ ጥቃቱ የመስጂዱን ጣሪያና ግድግዳ ማፈራረሱን ተከትሎም በርካታ ሰዎችን ከፍርስራሹ የማውጣቱ ስራ ቀጥሏል ነው ያሉት የፔሽዋር ከተማ ፖሊስ አዛዥ ሊጃዝ ካህን።
የጥቃቱ አላማ እስካሁን ባይታወቅም የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃቱ በመስጂዱ ቅጥር ውስጥ መፈጸሙን ነው አዛዡ የተናገሩት።
ከሟቾቹ ውስጥ በርካታ ፖሊሶች ያሉበት ከመሆኑ አንጻር ግን የጸጥታ ሃይሎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው።
የአጥፍቶ መጥፋት የቦምብ ጥቃቱ ሲፈጸም ከ300 በላይ የፖሊስ አባላት በስፍራው እንደነበሩም ሊጃዝ ካህን ገልጸዋል።
ለጥቃቱ እስካሁን ሃላፊነት የወሰደ አካል አለመኖሩን የሬውተርስ ዘገባ አመላክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሻባዝ አሪፍ ጥቃቱን ያወገዙ ሲሆን፥ ሁሉም ፓኪስታናዊ በሽብርተኞች ላይ በአንድነት እንዲሰለፍ አሳስበዋል።
በፔሽዋር ከተማ የሚገኘው ሌዲ ሪዲንግ ሆስፒታል፥ በቦምብ ጥቃቱ የቆሰሉ ሰዎችን ለማትረፍ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝና ዜጎች በፍጥነት ደም እንዲለግሱ መጠየቁ ተገልጿል።
በመዲናዋ ኢስላማባድም ሁሉም የጸጥታ አካላት በተጠንቀቅ ላይ ሆነው ከተማዋን ከሽብር ጥቃት እንዲጠብቁ ታዘዋል ነው የተባለው።
በፔሽዋር ከተማ ባለፈው አመት መጋቢት ወር በሺያ መስጂድ ላይ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ነው።
በወቅቱ አይ ኤስ ለጥቃቱ ሃላፊነቱን መውሰዱ አይዘነጋም።