ኢራን እና ሩሲያ ያክሆንት የተሰኘውን ሚሳኤል ለሁቲ አማጺያን ለማስታጠቅ እየመከሩ ነው ተባለ
የሁቲ አማጺያን ሩሲያ ሰራሽ ሚሳኤል ከታጠቁ ቀይ ባህር የበለጠ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ተገልጿል
አሜሪካ የኢራን እና ሩሲያ ድርድር አሳስቧታል ተብሏል
ኢራን እና ሩሲያ ያክሆንት የተሰኘውን ሚሳኤል ለሁቲ አማጺያን ለማስታጠቅ እየመከሩ ነው ተባለ፡፡
ከ11 ወራት በፊት የፍልስጤሙ ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ ነበር በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት የተቀሰቀሰው፡፡
እስራኤል ሐማስ በሚንቀሳቀስበት ጋዛ ውስጥ ባደረሰችው ጥቃት ከ41 ሺህ በላይ ንጹሃን የተገደሉ ሲሆን አሁን ደግሞ ይህ ጦርነት ወደ ሊባኖስ ዞሯል፡፡
ከሂዝቦላህ በተጨማሪ የየመኑ ሁቲ አማጺ ቡድ ከፍልስጤማዊያን ጎን እንደሚቆም መግለጹን ተከትሎ እስራኤል እና አሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸው የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ላይ ይገኛል፡፡
አሜሪካ እና ብሪታንያ በየመን የሁቲ አማጺያን ይዞታዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ቢያደርሱም በቀይ ባህር በሚያልፉ መርከቦች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ሊቆም አልቻለም፡፡
አሁን ደግሞ ሩሲያ ለዚሁ ቡድን ያክሆንት የተሰኘውን ሚሳኤል እንድትሰጥ ኢራን እያደራደረች እንደሆነ ተገልጿል፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ኢራን ሩሲያን እና የሁቲ አማጺንን እያግባባች ነው የተባለ ሲሆን እስካሁን በቴህራን የሩሲያ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና አማጺያኑ ሁለት ጊዜ ተሰብስበዋል፡፡
ያክሆንት የተሰኘው ሚሳኤል በሁቲ አማጺያን እጅ ላይ ከገባ በቀይ ባህር ትራንስፖርት የሚልፉ መርከቦች በቀላሉ ለጥቃት ይጋለጣሉ የተባለ ሲሆን የምዕራባዊን መርከቦች ደግሞ የበለጠ ለጥቃት ይጋለጣሉም ተብሏል፡፡
ሩሲያ ከዚህ በፊት ይህንን ሚሳኤል ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው ሂዝቦላህ ሰጥታለች የተባለ ሲሆን አሁን ደግሞ ለሁቲ አማጺያን ለመስጠት ውይይቶች በመደረግ ለይ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
አሜሪካ የኢራን እና ሩሲያ ወታደራዊ ትብብር እየጨመረ መምጣት እንዳሳሰባት በተደጋጋሚ የገለጸች ሲሆን ያክሆንት ሚሳኤል ለሁቲ አማጺያኝ ከተሰጠ ጉዳዩን በቀላሉ እንደማትመለከተው በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡