ኢትዮጵያ 190 ሺህ ፓስፖርት ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባቷን ገለጸች
ኢትዮጵያ የመዳረሻ ቪዛን ከመስከረም ጀምሮ መስጠት እንደምትጀምር ገለጸች
ከፓስፖርት ጋር በተያያዘ ያሉ የሌብነት ስራዎችን ለማስቀረት እርምጅ በመውሰድ ላይ እንደሆነም ተገልጿል
ኢትዮጵያ 190 ሺህ ፓስፖርት ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባቷን ገለጸች፡፡
በአገልግሎት አሰጣጡ ምክንያት ሁሉንም ከፍተኛ አመራሮች ከሀላፊነት በማንሳት አዲስ አመራር የተሾመለት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የተለያዩ ማሻሻያዎችን በመውሰድ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ላይ ተቋሙን በሀላፊነት እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር) የተሾሙት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ በመግለጫቸው 300 ሺህ ዜጎች ፓስፖርት ለማግኘት ተመዝግበው እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል።
በፓስፖርት እጥረት እና በብልሹ አሰራር ምክንያቶች ዜጎች ሲንገላቱ ቆይተዋል ያሉት ዳይሬክተሯ 190 ሺህ ፓስፖርት በአንድ ወር ውስጥ በውጭ ሀገር ታትሞ ወደ ሀገር ቤት ገብቷልም ብለዋል፡፡
ተቋሙ አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ የተለያዩ ዘመናዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆኑን ገልጸው ከዚህ በፊት ለዜጎች እንግልት መነሻ የሖኑ ደላሎች ፣ ህገ ወጥ አሰራር ላይ የተሳተፉ ሰራተኞች እና ሌሎች አካላት በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ፖስፖርት ማግኘት ቅንጦት ሆኗል ሲሉ ተገልጋዮች ተናገሩ
ወ/ሮ ሰላማዊት አክለውም ፓስፖርት ለመውሰድ ከተመዘገቡ ከስድስት ወር በላይ ለሆናቸው ዜጎች በቅድሚያ ፓስፖርት እንደሚሰጡ ጠቅሰዋል፡፡
የፓስፖርት ቀጠሮ ያለፈባቸው አገልግሎት ፈላጊዎች ዘወትር ቅዳሜ እየመጡ መስተናገድ ይችላሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ ወደ ሀገር ውስጥ ከገባው ፓስፖርት በተጨማሪ ፓስፖርት ለማግኘት በዉጪ ከሚገኝ አምራች ተቋም ጋር ከስምምነት መድረሳቸዉን ጠቅሰዋል።
ወደ ሀገር ውስጥ የገባውን ፓስፖርት በውጪ ሀገራት ላሉ ኢትዮጵያዊያን ቅድሚያ በመስጠት ቀስ በቀስ ለፓስፖርት ፈላጊ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ይሰጣልም ተብሏል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለም ኢትዮጵያ የመዳረሻ ወይም አራይቫል ቪዛን ከመስከረም ጀምሮ መስጠት እንደምትጀምር ወ/ሮ ሰላማዊት ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት ለውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ከሁለት ዓመት በፊት መስጠት የጀመረች ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ እና በሌሎች ምክንያቶች ተቋርጦ ቆይቷል፡፡
የጎብኚዎችን ቁጥር ከፍ እንደሚያደርግ የሚገለጸው የመዳረሻ ቮዛ አገልግሎት ከመስከረም 15 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡