ዩክሬን በግዛቷ ውስጥ የሩሲያ ዜግነት መሰጠት መጀመሩን አውግዛለች
በሩሲያ ቁጥጥር ስር በዋሉ ሁለት ዩክሬን ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ባለስልጣናት የሩሲያን ፓስፖርት መስጠት መጀመራቸው ተገለፀ።
የሩሲያን ፓስፖርት መስጠት የተጀመረው በኬርሶንና ማሪፑል ከተሞች መሆኑን የታስ ዘገባ ያመለክታል።
በትናትናው እለት በተጀመረው ስነ ስርዓትም 23 የኬርሶን ከተማ ነዋሪዎች የሩሲያን ፓስፖርት መቀበላቸውን ታስ አስነብቧል።
የሩሲያ ፓስፖርት ለመውሰድም በኬርሶንና ማሪፑል ከተሞች የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ማመልከታቸውም እየተነገረ ይገኛል።
በኬርሰን ውስጥ በሩሲያ የተሾመው ወታደራዊ አስተዳዳሪ ቮሎዲሚር ሳልዶ፤ "በኬርን የሚገኙ ሁሉም ጓዶቻችን በተቻለ ፍጥነት ፓስፖርት እና የሩሲያ ዜግነት መቀበል ይፈልጋሉ" ብለዋል።
ዩክሬንበበኩሏ “ሩሲያ እያደረገችው ያለው ተግባር በግዛቴ ውስጥ የሩሲያ ዜጎች መፈጠር ነው” በማለት ማውገዟም ተስመቷል።
ሩሲያ በዩክሬን ግዛት ውስጥ ፓስፖርት መስጠት መጀመሯ የዩክሬንን የግዛት እንደነት የሚፈታተን እና ዓለም አቀፍ ህጎችን የጣሰ መሆኑንም አስታውቃለች።
በቅርቡም የመጀመሪያው የሩሲያ ባንክ በሩብል መገበያየትና የሩሲያን የቴሌኮምና ሌሎችንም አገልግሎቶች መጠቀም በጀመረው የኬርሶን አካባቢ በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር የአካባቢው የአስተዳደር አካላት ማስታወቃቸው ይታወሳል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዘመናዊቷ ሩሲያ ዕጣ ፋንታ የሚወሰነው የቀድሞ ግዛቶቿን መመለስና ማጠናከር መሆኑን ማስታወቃቸውም አይዘነጋም።
ሩሲያ በዩክሬን ጀመርኩት ያለችው “ወታደራዊ ተልዕኮ” የሚጠናቀቀው ግቡን ሲመታ መሆኑን አስታቀውቃለች። የሩሲያ ቤተ መንግስት (ክሬምሊን) ቃለ አቀባይ ዲሚትሪ ፒስኮቭ ፕሬዝዳንት ፑቲን ለተልዕኮው አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን መዘርዘራቸውን ገልጸዋል።
ምንም እንኳን ሩሲያ ወታደራዊ ተልዕኮ እያደረገች መሆኑን ብትገልጽም ምዕራባውያን ግን ሩሲያ ዩክሬንን እንደወረረች እየገለጹ ነው። ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ ከገቡ 100 ቀናት አልፈዋል።