በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት በትንሹ 54 ሰዎች መገደላቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገልጿል
የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ ባለሥልጣን የኢትጵያ ጉዳይ እግጅ አሳሳቢ ነው አሉ
የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና የሕብረቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቦሬል ፎንትለስ በኢትዮጵያ ያለው አሁናዊ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን አስታወቁ፡፡
በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው የነበሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ በሀገሪቱ ያሉ አለመረጋጋቶች ትልቅ የሥጋት ምንጭ መሆናቸው ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ጎረቤት ሀገራት በሀገሪቱ ያለው ውጥረት እንዲረግብ ማደረግ አለባቸውም ሲሉ ነው በመግለጫቸው የጠየቁት፡፡
ሁሉንም ወገኖች ያካተተ ብሔራዊ መግባባት ማምጣት እንደሚገባ የገለጹት ኃላፊው ይህን ማድረግ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ያስፈልጋል ብለዋ፡፡
ሁሉንም የሚመለከታቸውን የፖለቲካ ኃይሎች ማሳተፍና ውይይት ማድረግ ለዴሞክራሲና ለቀጣው የሕዝብ ብልጽግና ወሳኝ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ ያለውን የሪፎርም እርምጃ እንደሚደግፍና ለዚህም የሕግ የበላይነትን ማስከበር እንዲሁም የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ማስከበር ቀዳሚው ነው ብለዋል፡፡ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ማስከበር እንደሚገባ ያነሳው የአውሮፓ ሕብረት ይህን ማድረግ ቀጣዩን ምርጫ ነጻ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ አድርጎ ለማጠናቀቅ ያግዛል ብሏል፡፡
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት ቢያንስ 54 ሰዎች በአማራነታቸው ተለይተው መገደላቸውን ገልጿል፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የሟቾች ቁጥር 32 መሆኑን መግለጹ ይታወቃል፡፡
አምነስቲ ባወጣው መግለጫ ጥቃቱን “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት “ እንደፈጸመው እንደሚገመት ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሳይጠበቅና ምክንያቱን ሳያሳውቅ ከስፍራው መውጣቱን ተከትሎ ወዲያውኑ ጥቃቱ መፈጸሙን አምነስቲ ጠቅሷል፡፡
ድርጅቱ “ትርጉም የለሽ” ያለውን ይህንን ጥቃት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲያጣራ እና ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠይቋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረትም የተፈጸመውን የግድያ ወንጀል አውግዟል የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ባወጡት መግለጫ የንጹኃንን ግድያ ያወገዙ ሲሆን ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
የሀገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ብሔራዊ ምክክር ሊያደርጉ እንደሚገባ ያሳሰቡት ሊቀመንበሩ በዚህም ብሔራዊ መግባባት ሊፈጠር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አጠቃላይ ቀጣናው ወደ ቀውስ ሊያመራ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት በኢትዮጵያ የሚከናወነውን የሪፎርም ጉዞ እንዲሁም ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍም ሙሳ ፋኪ ገልጸዋል፡፡