“የሱዳን ሽግግር በቀጣናዊ ውጥረቶች ምክንያት እንዲደናቀፍ አንፈቅድም”- ጆሴፕ ቦሬል፣ የአውሮፓ ህብረት ምክትል ፕሬዝዳንት
በኢትዮጵያ ካሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ያደርግ የነበረውን የበጀት ድጎማዎችን ሊያቆም እንደሚችል ማስታወቁ አይዘነጋም
ህብረቱ “ታሪካዊ” ያለው የሱዳንን ሽግግር ተቀዳሚ አጀንዳው መሆኑን አስታውቋል
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ እና ደህንነት ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፕ ቦሬል ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ጋር በስልክ ማውራታቸውን አስታወቁ፡፡
ቦሬል “ታሪካዊ” ያሉት የሱዳንን ሽግግር የህብረቱ ተቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም “ሽግግሩ በወቅታዊ ቀጣናዊ ውጥረቶች ለአደጋ መጋለጡን አንፈቅድም”ም ነው ምክትል ፕሬዝዳንቱ ያሉት፡፡
ቦሬል በኢትዮጵያ ስላለው “አሳሳቢ ሁኔታ” በተደጋጋሚ ሲገልጹ እና ሲያወግዙ ይስተዋላል፡፡
በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ስላለው የድንበር ጉዳይ እንዲወያዩ እና በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲገመግሙ የፊንላንዱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሃቪስቶን ልዩ መልዕከተኛ አድርገው ልከው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሃቪስቶ ከሱዳን እና ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ተወያተው እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ደጋጋሞ መግለጫ ያወጣው ህብረቱን ድጋፍ እስከማቋረጥ የሚደርስ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችልም ሲያስታውቅ ነበረ፡፡
ሆኖም ኢትዮጵያ የህብረቱን መግለጫ አውግዛለች፡፡ በመካከላቸው ያለውን አጋርነት ከማጠናከር ይልቅ ሊጎዳው እንደሚችልም ነው በወቅቱ ያስታወቀችው፡፡