የአውሮፓ ህብረት የፊንላንዱን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ሊልክ ነው
ህብረቱ ትናንት ኤርትራን ጨምሮ በምያንማር፣ ቻይና እና ሩሲያ ላይ ማዕቀብ መጣሉን ማስታወቁ የሚታወስ ነው
ፔካ ሃቪስቶ በኢትዮጵያ እና በቀጣናው ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በድጋሚ ያጤናሉ፤ ይመካከራሉም ተብሏል
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ እናየደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ኮሚሽነር ጆሴፕ ቦሬል የፊንላንዱን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሃቪስቶን በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልኩ አስታወቁ፡፡
የህብረቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ቦሬል ሃቪስቶን በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ የሚልኩት በኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲያጤኑ ነው፡፡
ይህንንም ቦሬል ትናንት በቤልጂዬም ብራሰልስ መሰብሰብ ለጀመረው የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ምክር ቤት አሳውቀዋል፡፡
ተልዕኮውን ተቀብለው ዳግም ወደ ኢትዮጵያ እና ወደ ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ለመጓዝ ያላቸውን ዝግጁነት የገለጹት ሃቪስቶም “ግጭቶችን ለማብረድ፣ ያልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረግ እና የመብት ጥሰት ምርመራዎችን ለማድረግ መወያየቱ ይጠቅማል” ሲሉ በትዊተር የማህበረሰብ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
ሃቪስቶ ከአሁን ቀደም በቦሬል ላኪነት በሱዳንና በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ በትግራይ ክልል እና በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ከፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና ከሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ጋር ተወያይተዋል፡፡
በአውሮፓ እና በአፍሪካ ህብረት መካከል ስላለው ግንኙነት ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጋር መምከራቸውም ይታወሳል፡፡
ሃቪስቶ በካርቱም በነበራቸው ቆይታ ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር መክረው ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውም ይታወሳል፡፡
ህብረቱ ትናንት ኤርትራን ጨምሮ በምያንማር፣ ቻይና እና ሩሲያ ላይ ማዕቀብ መጣሉን ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
የአውሮፓ ህብረትን መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሃገራት በትግራይ ክልል የከፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ሌሎችም ሁኔታዎች እንዳሉ በመጥቀስ ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
“ስጋቱ ትዊተር ላይ ብቻ መቅረት የለበትም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ በነበራቸው የምክር ቤት ቆይታ “ስጋት አለን የሚሉ አካላት ስጋታቸውን ከመግለጽ ባለፈ የእርዳታ እጆቻቸውን በወጉ እንዲዘረጉ” መጠየቃቸው የሚታወስ ነው፡፡