ሽልማቱ በተለይ ከ2009 ወዲህ የሜሲ እና ሮናልዶ ብቻ መስሏል
በፈረንጆቹ 1956 በፈረንሳይ የተጀመረው የባሎንዶር ሽልማት በየአመቱ የተለየ ብቃት ያሳዩ የእግር ኳስ ተጫዋቾች የሚወስዱት ትልቅ ክብር የሚሰጠው ሽልማት ነው።
እንግሊዛዊው ስታንሊ ማቲውስም የመጀመሪያው የባሎንዶር ተሸላሚ ሆኗል።
አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ እና የፖርቹጋሉ የእግር ኳስ ፈርጥክርስቲያኖ ሮናልዶ ስምንት እና አምስት ጊዜ ይህን ሽልማት በመውሰድ ስማቸውን በጉልህ አጽፈዋል።
የሜሲ የሀገር ልጅ ዲያጎ ማራዶናም ሆነ ብራዚላዊው ፔሌ ግን ይህን ሽልማት መውሰድ አልቻሉም።
የ20ኛው ክፍለ ዘመን የእግር ኳስ ፈርጦች ባላንዶር ለምን አልተሸለሙም?
የባሎንዶር ሽልማት እስከ ፈረንጆቹ 1995 ድረስ ለአውሮፓ ተጫዋቾች ነበር የሚሰጠው፤ ከሌላ አህጉር በአውሮፓ የሚጫወቱ ተጫዋቾች በዚህ ሽልማት እጩ ሆነው አይቀርቡም ነበር።
ፔሌ እና ማራዶና ባሎንዶር የባሎንዶር ማሻሻያም ሆነ የ1991ዱ የፊፋ የአመቱ ምርጥ ተጫዋቾች ምርጫም አልፏቸዋል።
ከ15 አመቱ ጀምሮ ለብራዚሉ ሳንቶስ የተጫወተው ፔሌ በአውሮፓ አልተጫወተም። ከፈረንጆቹ 1956 እስከ 1974 በነበረው የሳንቶስ ቆይታ 605 ጊዜ ተሰልፎ 1218 ጎሎችን አስቆጥሯል።
ብራዚላዊው ማራዶና በበኩሉ ባርሴሎና፣ ሲቪያ እና ናፖሊን ለመሳሰሉ የአውሮፓ ክለቦች ቢጫወትም የባሎንዶር የሽልማት ቅድመ ሁኔታ ሲሻሻል ጨዋታ አቁሟል።
በ21 አመታት የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋችነት ህይወቱ 490 ጊዜ ተሰልፎ 259 ጎሎችን ያስቆጠረው ማራዶና ለሀገሩ አርጀንቲናም 34 ጎሎችን በማስቆጠር የክፍለዘመኑ ምርጥ ተጫዋች ነው ቢባልም ባሎንዶር ሳይሸለም ቀርቷል።
የሃንጋሪው የምንጊዜም ምርጥ አጥቂ ፑሽካሽ፣ ሆላንዳዊው ፍራንክ ሪያካርድ፣ ጣሊያናዊው የኤሲ ሚላን ኮከብ ፓውሎ ማልዲኒ፣ የባርሴሎናው ቁልፍ አንድሬስ ኢኔስታ፣ ቴሪ ኦነሪ፣ ጂሊያሉጂ ቡፎን እና ኦሊቨር ካህን ይህን አለማቀፍ ሽልማት አለመውሰዳቸው በርካቶችን ያስቆጫል።
ሽልማቱ በተለይ ከ2009 ወዲህ የሜሲ እና ሮናልዶ ብቻ የመምሰሉ እና የምርጫው አወዛጋቢነት ጋር ተዳምሮ የባሎንዶርን ተቀባይነት እያደበዘዙት ነው የሚሉ አካላትም ተበራክተዋል።
ባሎንዶር ከፈረንጆቹ 2010 በኋላ ከፊፋ የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማት ጋር ተጣምሮ የፊፋ የባሎንዶር ሽልማት መባሉ የሚታወስ ነው።