የማንቸስተር ሲቲው ኧርሊንግ ሃላንድ የአመቱ ምርጥ ጎል አስቆጣሪ ክብርን ተቀዳጅቷል
የአመቱ የአለማችን ኮከብ ተጫዋች ይፋ የሚደረግበት ተጠባቂው የባሎንዶር ሽልማት ትናንት ማምሻውን በፈረንሳይ ተካሂዷል።
አርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ ለስምንተኛ ጊዜ የባሎንዶር ሽልማት የወሰደባት ፓሪስ ደምቃ አምሽታለች።
በኳታር ሀገሩን ከ1986 በኋላ የአለም ዋንጫ ሻምፒዮን ያደረገው ሜሲ ከ2021 በኋላ ሽልማቱን ዳግም በእጁ አስገብቷል።
በሴቶች ደግሞ የባርሴሎና ተጫዋቿ አኒታ ቦናቲ የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ሆና ተመርጣለች።
የሜሲ ዋነኛ ተፎካካሪ የነበረው የማንቸስተር ሲቲ አጥቂ ኧርሊንግ ሃላንድ የአመቱ ምርጥ ጎል አስቆጣሪ ተብሎ ተሸልሟል። ሃላንድ በውድድር አመቱ 56 ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን ከሲቲ ጋር ሶስት ዋንጫዎችን ማንሳት መቻሉ ይታወሳል።
አርጀንቲናዊው የአስቶንቪላ ግብ ጠባቂ ኢሚሊያኖ ማርቲኔዝ ደግሞ የአመቱ ምርጥ ግብ ጠባቂ ሆኖ በመመረጥ ሽልማቱን ወስዷል።
እንግሊዛዊው አማካይ ጁድ ቤሊንግሃም የ2023 የአለም ምርጥ ወጣት ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል።
ብራዚላዊው የሪያል ማድሪድ ተጫዋች ቪኒሽየስ ጁኒየር ደግሞ በሰብአዊ ስራው የአመቱ ተሸላሚ ሆኗል። ዘረኝነትን መዋጋቴን እቀጥላለሁ ያለው ተጫዋቹ በብራዚል ገጠራማ ስፍራዎች ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ለበርካቶች የትምህርት እድል ፈጥሯል።
ማንቸስተር ሲቲ እና ባርሴሎና (የሴቶች ቡድን) የአመቱ ምርጥ ክለብ ሆነው ሽልማት ወስደዋል።